HR 6600 ሰነድ በእነ ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ የተጀመረውን የሰላም እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል ተባለ

የካቲት 10/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያሰናዳው የHr 6600 ሰነድን በ#no more ወይም በቃ እንቅስቃሴ ተቃውሞ እንደገጠመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ በተለይም HR 6600 ሰነድ በእነ ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ የተጀመረውን የሰላም እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ፀሐፊ አሚና መሀመድ አሸባሪው ሕወሓት በአፋር እና በአማራ ክልል ያደረሰውን ውድመት ከተመለከቱ በኋላ ድርጅቱ በእነዚህ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመርዳት እንደሚሰራ መግለፃቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ድርቅ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ለመርዳት እና እንዲያገግሙ ለማድረግ ይሰራል ማለታቸውንም አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውም ተነግሯል።

በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው መቀጠል በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ዙሪያ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በጋራ መሥራት እና የጋራ ተጠቃሚነታቸው ላይ ነው በትኩረት ውይይት መደረጉን ነው ቃል አቀባዩ የገለፁት።

ኢትዮጵያ እና ኬኒያ የኢነርጂ ወይም የኤሌክትሪክ ሽያጭ ላይ ስምምነት ማድረጋቸውም በመግለጫው ተገልጿል።

በሳኡዲ አረቢያ በችግር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ በቅርቡ በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የተመራ ልኡካን ቡድን ወደ ሳኡዲ በማምራት በዜጎች ሰብዓዊነት ዙሪያ የተወያዩ መሆኑንና ዜጎችን መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም አምባሳደሩ አስታወቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሥራው በፍጥነት ተግባራዊ አለመሆኑን ጠቁመው ዋናው መሠራት ያለበት በአገር ውስጥ በሚደረገው ህገወጥ ስደት ማስቀረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።