ህብረተሰቡ ራሱን ከስትሮክ ህመም መጠበቅ እንደሚገባው ተገለጸ

ጥቅምት 18/2014 (ዋልታ) የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) ህመም አስከፊነት በአግባቡ ግንዛቤ በመያዝ ህብረተሰቡ ራሱን መጠበቅና መከላከል እነደሚገባው አሳሰቡ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 13 ነጠብ 7 ሚሊየን ሰዎች በስትሮክ ሳቢያ ለህመም እንደሚዳረጉ የገለፁት ዶ/ር ደረጀ የህመሙን አስከፊነት በአግባቡ ግንዛቤ በመያዝ ህብረተሰቡ ራሱን መጠበቅና መከላከል አለበት ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር ስትሮክን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችን በብዛት በማሰልጠን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲሰጡ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ሚኒስትር ድኤታው ጠቁመዋል።
በሽታውን ለማከም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ደረጀ መንግስት በተቻለ መጠን መድሃኒቶችን እና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በየጤና ተቋማቱ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኒዩሮሎጂስቶች ማህበር ጸሐፊ ዶክተር ሜሮን አውራሪስ በበኩላቸው የዓለም የስትሮክ ቀን በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፊታችን አርብ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ይከበራል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ከስትሮክ ራሱን ለመጠበቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የስብ መጠንን ማስተካከል እንዲሁም አስፈላጊውን የጤና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።