ህወሃት የተጠና ዘረፋና ውድመት መፈጸም

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል ያደረገው ዘረፋና ውድመት በታቀደና በተጠና መንገድ መካሄዱን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው በአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በትግራይ ወራሪ ኃይል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ቁሳዊ ውድመቶች እና ያስከተለው ሁለንተናዊ ቀውስ የሚል ርዕስ ሰጥቶ ያወጣው ጥናት እንደሚያመለክተው አሸባሪ ቡድኑ ጦርነቱ የመላው ትግራይ ነው በማለት ለዘጠኝ ቀናት ያልተቋረጠ ወረራ ፈጽሟል።

ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው ከተማዎች፣ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች የማሸበር፣ የማግባባት፣ የመዝረፍና የማውደም ስልቶች መተግበሩን ጥናቱ አመልክቷል።

“በየቤቱ በመሄድ የነዋሪዎችን በር አስከፍቶና ሰብሮ በመግባት ብርበራ በማካሄድ፣ የጦር መሳሪያዎችን፣ ዋጋ የሚያወጡ ውድ ንብረቶችን ወርሷል” ያለው ጥናቱ፤ ከዝርፊያ የተረፉትንና ለዝርፊያ የማይመቹ ቁሳቁሶችን ደግሞ ከጥቅም ውጭ አድርጎ ማውደሙን ጠቁሟል።

“የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በማውደሙ፣ ዜጎች ጥረው ግረው ያገኙት ሀብትና ንብረት ላይ ሁለንተናዊ ዝርፊያና ውድመት በመፈፀሙ የዜጎችን ራእይ እንዲጨልም አድርጓል” ብሏል ጥናቱ።

የተፈጸመው የቡድኑ ዘረፋና ውድመት በቅድመ ዝግጅት የተከናወነ ስለመሆኑ በርካታ አመላካቾች እንዳሉ ማስታወቁን ከኢዜአ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።