ህወሓት ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት መጋዘኖችን መዝረፉን ድርጅቱ ገለፀ

ነሃሴ 25/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት መጋዘኖችን እንደዘረፈ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ሚሽን ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) የኢትዮጵያ ሚሽን ዳይሬክተር ሾን ጆንስ ህወሓት ሁኔታውን ያለአግባብ እየተጠቀመበት እንደሆነ እናምናለን ብለዋል፡፡
ከተረጂዎች ላይ እርዳታን በሃይል እየነጠቀ እንደሆነ ይሰማናል ያሉት ዳይሬከተሩ፣ እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ግን የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያሉትን የእርዳታ መጋዘኖቻችንን ዘርፈዋል፡፡
የህወሓት ወታደሮች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል፣ መኪኖችን ሰርቀዋል በየመንደሮቹ ብዙ ውድመትን አድርሰዋል ብለዋል፡፡
ይህ ደግሞ ለተጎጂዎቹም ሆነ ለእኛ ለረጂዎቹ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ ማስረዳታቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አጋሮቻችን መካከል አንዷ ነች ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለን አጋርነት በእጅጉ እንጨነቃለንም ብለዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ህብረተሰቡ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩትን ያልተረጋገጡ ወሬዎች በመያዝ የኢትዮ አሜሪካ ግንኙነት እንደሻከረ ያስባሉ ያሉት ጆንስ፣ ነገር ግን እንደአሁኑ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብረን የሰራንበት ጊዜ የለምም ነው ያሉት፡፡