ነሀሴ 17/2013 (ዋታል) –በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ የደረሰው ከፍተኛ ኪሳራ የድሉን አይቀሬነት ከወዲሁ እያበሠረ እንደሚገኝ የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ አስታወቁ፡፡
ዳይሪክተሩ በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ሕልውናችንን እና ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር የገባንበት ጦርነት ፍጻሜው የሚወሰነው በሕልውናችን እና በሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ ሆኖ የተጋረጠው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ ከኢትዮጵያ ሲጠፋ ብቻ ነው ብለዋል።
አቶ ግዛቸው በወቅታዊ ጉዳይ ያጋሩት ሙሉ መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ እያደረስነው ያለው ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ የድላችንን አይቀሬነት ከወዲሁ እያበሠረን ይገኛል፡፡
ሕልውናችንን እና ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር የገባንበት ጦርነት ፍጻሜው የሚወሰነው በሕልውናችን እና በሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ ሆኖ የተጋረጠው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ ከአማራ/ ከኢትዮጵያ ሲጠፋ ብቻ ነው፡፡
ይህን ሽብርተኛ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ጠርጎ ለማስወገድ እያደረግነው ያለው ጦርነት አሸናፊነታችን የሚመዘነው አነስተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ መስዋእትነት በመክፈል አሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድቀት በማድረስ ቡድኑን ለዘላለሙ እንዳያንሰራራ በማድረግ እና ባለማድረግ ብቃታችን ብቻ ነው፡፡
ከዚህ መስፈርት አንጻር ባለፉት ቀናት ውስጥ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራ እና ከመላው ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡት የልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች እና እንዲሁም ሀቀኛ ፋኖዎቻችንና በየአውደ ውጊያው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችና ወጣቶች በአሸባሪው የትህነግ ታጣቂዎች ላይ እያደረሱት ያለው የሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ሲታይ በጠላታችን ላይ ድል እየተቀዳጀን መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው በተለይም ወደ ተሟላ ጦርነት በገባንባቸውና የጠላት ኃይል የተለዬ ትኩረት ባደረገባቸው በማይጠብሪ፣ በጋይንት፣ በጋሸና፣ በመርሳ፣ በወልድያ አከባቢ፣ በደብረ ዘቢጥ እና አካባቢዎች ላይ አስገድዶ ባዘመተብን የጠላት ኃይሎች ላይ ጀግኖቻችን በወሰዱት የማጥቃት ዘመቻ በእያንዳንዷ ቀን እንደ የጠላት ኃይል ተገቢውን ቅጣት እየተሰጣቸው እንደቅጠል እየረገፉ ይገኛሉ፡፡ ጠላት ኃይልም ከገባበት የአማራ መሬት እንዳይወጣ ተደርጎ በወዳጅ የጦር ኃይለሰ እየተወገረ ይገኛል።
“ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” እንዲሉ አበው ከሞት የተረፉት ደግሞ ቁስለኞች ሆነው እጆቻቸውን እያርገበገቡ የምርኮኝነት ጸጋን ለማግኘት እየተማጸኑ የመሆናቸውን ሀቅ ምስክርነት ለማራኪዎቹ ጀግኖቻችን እና ለተማራኪዎቹ ባንዳዎች እንተወዋለን፡፡
ይሁን እንጂ ጀምበር ወጥታ በጠለቀችበት በእያንዳንዷ ቀን እንደ እባብ አናቱን እየተቀጠቀጠ የሚገኘው የትህነግ ሽብርተኛ ቡድን መሰሪ ክፋት አኳያ አሁን እየወሰድንበት የሚገኘው የማያዳግም እርምጃን አጠናክረን ከማስቀጠል በስተቀር በድል አድራጊነት ስሜት ልንቀዛቀዝ አይገባም፡፡
የጀመርነው ትግል ዓላማችን እስኪሳካ የበለጠ እየጋለ የሚሄድ እንጅ ያሰብነውን ግብ አሳክተን የጋራ ድላችንን በጋራ እስክናበስር በምንም ምክንያት አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የሚሄድ አይደለም።
እናም ጠላት ላይ እያደረግን ያለነው የህልውና፣ የፍትህና የነፃነት ዘመቻ የማጥቃት ማርሹን እየጨመረ በፍጥነት መጓዝ ይገባዋል። ይህ እንዲሆን በየተሰማራነበትና በተሰጠን ተልኮ ላይ አተኩረን ድምፃችንሰ አጥፍተን፤ የድርሻ የድርሻችንን እሌት ተቀን በተሟላ ሁኔታ መፈፀም ይገባናል።
ለአፍታም ቢሆን በምንም ምክንያት ለጋራ ጠላታችን መዘናጋትና መለሳለስ አይገባንም።
ይህ ሽብርተኛ ቡድን በወራሪነት በገባባቸው የክልላችን አንዳንድ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸማቸው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ግፎች ከአእምሮ በላይ ናቸው፡፡
የንጹሃንን ደም በማፍሰስ ያልተገደበው አሸባሪው የትህነግ ቡድን የደሃ አርሶ አደሮችን የጋማ እና የቀንድ ከብቶችን ጭምር የሚበላውን በልቶ፣ ጭኖ የሚወስደውን ወስዶ ያልቻለውን ደግሞ በተኩስ እሩምታ ፈጅቷል፡፡
በከተሞች ውስጥ ደግሞ በማኅበራዊ ተቋማት፣ በግለሰቦችና የመንግስት ንብረት ላይ የፈጸመው ውድመት መጠን ቡድኑን በቁሙ ከመቅበር በስተቀር የሚመጥነው የቅጣት እርምጃ ይኖራል ብሎ ለመገመት ያዳግታል፡፡ የትኛውንም የበደል ድርጊት ሁሉ በህዝባችን ላይ በግላጭ እየፈፀመው ይገኛል።
እናም ለዚህ ቡድን የሚራራ አማራና ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በእጃችን የገባው የአሸናፊነት ጉዟችንን ተራራ እና ሜዳ ከማስለቀቅ አኳያ ጊዜያዊ ድላችንን ሳንለካ ትኩረታችን ትህነግን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በሚደረገው ተጋድሎ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ በአሸባሪው ትህነግ ወረራ የተፈፀመባቸውን የአማራ አከባቢዎች ነፃ ማውጣትና ህዝባችንን ከሞትና ከዝርፊያ መታደግ መሰረታዊ ጉዳይ ቢሆን የሚከፈለውን የትኛውንም መስዋት ከፍለን በዘላቂነት አማራንና መላው ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላታችን አሸባሪው ትህነግ ነፃ በማውጣት ሰላም፣ ዴሞክራሲንና ብልፅግናን ማረጋገጥ ዋነኛ ግባችን መሆን ይገባዋል።
ተገደን የገባንበትን ትግላችንን የጀመርነው አሸባሪው ትህነግን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ነው። ትግላችንን የምናቆመውም በዓላማችን መሰረት ትህነግ ተንኮታኩቶ ሲቀበር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ዓላማ ውጭ የጀመርነውም ሆነ የምናቆመው ትግል አይኖረንም፡፡ ሊኖርም አይገባውም።
የትህነግ አጀንዳ መዘጋት የሚችለው ትህነግና ተከታይ የውጭና የውስጥ ባንዳና ተላላኪዎች እስከ ወዲያኛው ሲሸኙ ብቻ ነው። ግባችንም ይሄው ነው።
ማንኛችንም ኢትዮጵያውያን፤ በየትኛውም ቦታ፤ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነን ህልውና እና ሉዐላዊነታችንን ለማስጠበቅ እየተሳተፍንበት የምንገኘው ጦርነት ይህንን ዋና ዓላማ ለማሳካት እንጂ ለሌላ ስላለመሆኑ ቅንጣት ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም፡፡
ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መላውን ህዝብ ለዚህ ዓላማ በማደራጀት፤ በማንቃት እና በማስተባበር ሥራ ላይ ሊተጋ ግድ ነው። ሁሉም እንደየአቅሙ እና እንደየችሎታው ሚናውን ለይቶ አስተዋፅኦውን እንዲያበረክት ማስቻል ይገባል፡፡
የሚዲያ ተቋማት አሸባሪው የትህነግ ቡድን የፈፀማቸውን ሁለንተናዊ ኃጢአቶች በመሰነድ እውነታውን ለዓለም አደባባይ ማስጣት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ስለሆነም አሁን በሚዲያዎቻችን የተጀመረው ተጋድሎ ተጠናቅሮ ይቀጥላል።
በተለይም ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያ ጀግኖቻችን ከትህነግ ጀርባ መሽገው ሀገራችን ኢትዮጵያን በሀሰት ሲወነጅሉ የከረሙ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መሪዎች ላይ እውነቱን በማጋለጥ ያደረጋችሁት ርብርብና እየታየ የሚገኘው ውጤት ወደር የለውም፡፡ ይህ ውጤት የሚያሳየው የእኛ ኢትዮጵያውያን አይበገሬነት ምንጭ አንድነታችን መሆኑን ነው፡፡
አንድነታችንን አስጠብቀን በትናንሽ ድሎች ሳንኩራራ፤ በጥቃቅን ስህተቶች ሳንፈታ ትኩረታችንን ሳንስት በዋናው ዓላማችን ላይ ከተረባረብን በአጭር ጊዜ ውስጥ አሸባሪው ትህነግን ከምድረ ኢትዮጵያ ጠራርገን ማስወገድ እንችላለን፡፡
በአሁኑ ሰዓት የወገን ኃይል አስደማሚ ጀብዶችን እየፈጸመ፤ ገዢ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ መሆኑና የጠላት ኀይል ታጣቂዎች ቀን ከሌሊት እንደ ቅጠል እየረገፉ የተረፉትም በተበታተነ መልኩ በሽሽት ሩጫ ላይ መሆናቸው የድላችን አይቀሬነትን ከወዲሁ ያበስራል፡፡
አንድነታችንን ካስጠበቅን፣ በሚገባን ልክ ከተደራጀን፤ ትኩረታችንን በአላማችን ላይ ካደረግን ሁሌም አሸናፊዎች ነን።