በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ህግን ተላልፈው በተገኙ 46 የንግድና የማምረቻ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ባካሄደው ክትትልና ቁጥጥር ህግን ተላልፈው በተገኙ 46 ድርጅቶች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ እገዳ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሬ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተከተል ጌቶ ተናግረዋል፡፡
እርምጃ የተወሰደባቸው የንግድና የማምረቻ ድርጅቶች ከተሰጣቸው የንግድ ስራ ፈቃድ ዉጪና ባልታደሰ የንግድ ስራ ፈቃድ በመነገድ፤ በምርት ጥራት መጓደልና ብሄራዊ የምልክት አጠቃቀም መመሪያን ተግባራዊ ባለማድረግ ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
አሁን በደረስንበት የውድድር ሥርዓት ለማለፍ ጥራትን አስጠብቆ፣ ህግ እና አዋጅን አክብሮ መስራት ያሰፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የንግድ ድርጅቶችም ሆኑ የማምረቻ ተቋማት ይህንኑ ታሳቢ አድርገው ሥራቸውን በዲሲፒሊን መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለጥራት ብሎም ለአዋጆች ተግባራዊ መሆን ልዩ ትኩረተ ሰጥቶ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ተከተል፣ ህግና ሥርዓትን ተላልፈው የሚሰሩ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡