ህፃናትን በመስጠት ልምድ ያሳድጋል የተባለለት “የሚሰጥ ዘር ፕሮጀክት” ማጠቃለያ በአዳማ ይካሄዳል ተባለ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) ህፃናትን በመስጠት ልምድ ያሳድጋል የተባለለት “የሚሰጥ ዘር ፕሮጀክት” የዓመቱ ማጠቃለያ ፕሮግራም በአዳማ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የተያይዘን ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምስጋናው ታደሰ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ህፃናትን በመስጠት ልምድ የሚያሳድገውና ባለፉት አራት ወራት በአምስት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው “የሚሰጥ ዘር ፕሮጀክት” ከነሐሴ 25 እስከ 29 የመዝጊያ ፕሮግራሙን እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።

የቀድሞ የትምህርት ሚኒስቴር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እንዲሁም የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ መልካም ትብብር ተግባራዊ የተደረገው ፕሮጀክቱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ልጆችን በየሳምንተ ስጦታ እንዲሰጣጡና እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ሲያደርግ መክረሙንም አስታውሰዋል።

አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፣ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ፣ አርቲስት ሸዊት ከበደ እና አርቲስት ህፃን ማክቤልና ሌሎችም የበጎ ሀሳቡ ደጋፊዎች መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በአዳማ ከተማ ነዋሪውና የተያይዘን ኢትዮጵያ በመስራቹና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምስጋናው ታደሰ ሀሳብ ጠንሳሽነት ነው የተጀመረው፡፡

በሳራ ስዩም