ሆስፒታሉ በኦክስጅን እጥረት ታካሚዎችን ለመርዳት እንደተቸገረ ገለጸ

ሚያዚያ 14/2013 (ዋልታ) – የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ በኦክስጅን እጥረት ታካሚዎችን ለመርዳት እየተቸገረ መሆኑን ገለጸ።

የኦክስጅን ህክምናን በብዛት ከሚፈልጉ የጤና እክሎች መካከል በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋና ብዙዎችን ለከፋ የጤና ችግር ብሎም ለሞት እየዳረገ የሚገኘው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንዱና ዋነኛው ነው።

በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ ሲሆን የኦክስጂን ህክምና ፈላጊዎችም ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ለኮቪድ-19 ማገገሚያነት የተቋቋሙ ማእከላትም ሆኑ ሆስፒታሎች በየቀኑ በሚያስተናግዱት የኮቪድ-19 ታካሚዎች እየተጨናነቁና አስፈላጊውን ህክምና ለመስጠትም አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የኦክስጅን አጥረት ስለገጠመው ቀደም ሲል ለሌሎች ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን አቅርቦት አቋርጧል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የፋሲሊቲ መሃንዲስ አቶ ሰለሞን ሸዋንግዛው በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኦክስጅን እጥረቱ ሳቢያ ለሌሎች ሆስፒታሎች የሚሰጠው አቅርቦት ቀርቶ ለሆስፒታሉ ታካሚዎች በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አልቻለም።

“በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተባባሰና የታማሚዎች ቁጥርም እያሻቀበ በመምጣቱ ለኦክስጅን ፈላጊ ታካሚዎች ፈተና ሆኗል” ብለዋል።

እጥረቱን ለመፍታት በማእከሉ 24 ሰዓት እየተሰራ ቢሆንም ችግሩን ማቃለል አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል።