ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የሚንቀሳቀሰውን የድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ሃይል አባላት የሽኝት ተደረገላቸው

የድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ሃይል አባላት

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የሚንቀሳቀሰውን የድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ሃይል አባላት የሽኝት መርሃ ግብር ተደረገላቸው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የሰየመው የህውሀት ጁንታ ቡድን ሀገርን የማፈራረስና የመበታተን ተግባርና ተልእኮ የማምከንና ህግን የማስከበር ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ልዩ ሀይሎች ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ይገኛል።

ሀገራዊ ጥሪ በመቀበልም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የልዩ ሀይሎች በሀገራዊው ህግ የማስከበር ዘመቻ ለሚሳተፉ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ሀይል አባላት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና የካቢኔ አባላቶቻቸው፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ሀይል የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ በዘለለ ለሀገራዊ ጥሪው በአንድነት እንደቆመና ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከልዩ ሃይል ጎን እንደሆነና በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ሀገሪቱ የጠራችውን ታሪካዊ ጥሪ በመቀበልና የሀገሪቱን ሰላም ለመጠበቅና የህዝቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የተጀመሩ ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ እድገቶችም እንዲቀጥሉ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በጥሪው ላይ መሳተፍ እድለኛነትም ከመሆን ባለፈ ክብር መሆኑን ድሬዳዋ አስተዳዳር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሙሳ ጣሀ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ አደራ በመቀበል በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ በጀግንነት የሚጠበቅባቸውን ግዳጅ በመወጣት በድል እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የልዩ ሃይል አባላቱ በተሰማሩበት የሰላምና የፀጥታ ማስከበር ቦታዎች ላይ በታማኝነትና በቅንነት ግዳጃቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አመለክተዋል።

በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ኡጋዞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ የልዩ ሀይሉ አባላትም ከክብር እንግዶች እጅ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በክብር መረከባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡