ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊደረግ ነው

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊያደርግ እንደሆነ የከተማው የትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል በተባለው የድጎማ ሥርዓት በተጨማሪም በተሽከርካሪዎች ላይ GPS እንዲገጠም መደረጉ የትራንስፖርት ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ቁጥጥሩን ለማሳለጥ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተገለፀው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጐማ አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የነዳጅ ድጎማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሰጡ በታሪፍ እና በስምሪት ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ መለስተኛ እና መካከለኛ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተሸከርካሪዎችን የሚመለከት ይሆናል ተብሏል።
በዚህም የመንግሥትና የግል አውቶቡሶች፣ በከተማ ውስጥና በከተሞች መካከል የሕዝብ የትራንስፓርት አገልግሎት የሚሠጡ ኮድ 1 እና ኮድ 3 ሚኒባስ (አዲስ አበባ ውስጥ የተመዘገቡ) ተሽከረካሪዎችን ያካትታል።
እንደ ቢሮው ማብራሪያ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በግል እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሠራተኛ አገልግሎት እንዲሁም በግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ አገልግሎት የሚሠጡ ተሽከርካሪዎች በዚህ የታለመ የድጐማ አሰራር አይካተቱም።
በትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ጭነት ስምሪትና ድልድል ኦፕሬተር ፈቃድ ዳይሬክተር አልዓዛር ይርዳው ረቂቅ መመሪያው በአሁኑ ጊዜ እያደገ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሂደት በማስቀረት ወደ ቀደመው የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ሥርዓት እንዲመለስ ያስችላል ብለዋል።
በድጎማ ስርዓቱ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30/2014 ዓ.ም GPS መግጠም አስገዳጅ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸው እስከ ገንቦት 30/2014 ዓ.ም የተሸከርካሪዎች መረጃ ወደዳታ ቤዝ የማስገባት ስራ ይሰራል ብለዋል።
በመሆኑም በመዲናዋ በሕዝብ ትራንስፖርት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን የሚመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎች በአስር ቀናት ተደራጅተው ለቢሮው እንዲላኩ አሳስበዋል።