ለቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ተገለጸ

ጥር 24/2014 (ዋልታ) በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ተገለፀ።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች ጋር የተወያዩ ሲሆን ውይይቱም በተቋማት ተጠያቂነት፣ የመረጃ ፍሰትን ለመዘርጋት እንዲሁም ውጤታማ እና ቀልጣፋ ሥራ እንዲያከናወኑ ያስችላል በተባለ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ረቂቅ መዋቅር ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
በመንግሥትም ሆነ በግል የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ወደሚፈለገው ደረጃ ከፍ ለማድረግ በቀጣይ የትምህርት ዘመን የመውጫ ፈተና ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ሊሰጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርቱ ማኅበረሰብ ከፖለቲካ ነፃ ሆነው ሃሳባቸውን የሚያንሸራሸሩባቸው ተቋማት መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት፣ የምርምርና የአዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ ከመሆናቸው አንፃር ተልዕኳቸውን በብቃትና በውጤታማነት ለመፈፀም እንዲችሉ የተጀመረው የመዋቅር ሪፎርም ሥራ አንዱና ወሳኝ አካል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሕይወት ሊቀይሩ በሚቻሉበት መልኩ ከተልዕኳቸው ጋር አጠናክረው የሚሄዱበትን ጉዳይ ለይተው መሥራት እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡