ለተፈናቀሉ ወገኖች የ53 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ53 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ።
በሰቆጣ ከተማ በተደረገው ድጋፍ የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌውና የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው አሸባሪው የሕወሓት በአማራና በአፋር ሕዝብ ታሪክ ይቅር የማይለው ሰብኣዊና ቁሳዊ ጥፋት ማድረሱን አንስተዋል።
ሚኒስትሩ የዋግኽምራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ታሪክ ለፍትህና እኩልነት የታገለ፣ ለተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች የማይበገር ጽኑ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሕዝብ ሲቸገር ድጋፍ ስናደርግ ከፍ ያለ ሐሴት ይሰማናል ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ተቋማቱ እስካሁን ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ115 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርገዋል ማለታቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።