ለአርብቶ አደሩ አስፈላጊውን ዕገዛ በማድረግ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምክክር ይደረጋል

ጥር 16/2014 (ዋልታ) ለአርብቶ አደሩ አስፈላጊውን ዕገዛ በማድረግ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምክክር እንደሚደረግ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ 18ኛው የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ቀን በዓል አከበበር ላይ በሰጡት መግለጫ መስኖን በስፋት ማልማት በሚቻልበት መንገድ ላይ ጥናት እንደሚደረግ ጠቁመው በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች ድምፅ ለመሆን ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

በኦሮሚያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ክልል አካባቢዎች ድርቅ የተከሰተባቸው ሲሆኑ መንግስት ድጋፍ እያደርገ ነው ተብሏል።

ከችግሩ ለመውጣትና ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።

በዓሉ ከሁለት ዓመት በፊት በጅንካ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት በዓሉ በኦሮሚያ ክልል ኣዳማ ከተማ ይካሄዳል። ባለፈው ዓመት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዳልተከበረም ተጠቁሟል።