ለአሸባሪ ሸኔ ቡድን በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረ የብሬን ጥይት ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ዋለ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) ለአሸባሪው ሸኔ ቡድን እንዲደርስ ታስቦ በተሽከርካሪ ሲንቀሳቀስ የነበረ የብሬን ጥይት ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የዜጎች በሰላም ውሎ ማደር እንቅልፍ የሚነሳቸው ፀረ- ሰላም ኃይሎች የሚያደርጉትን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በፀጥታ ኃይሎች የሚደረገው ህግን የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ኅዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ጥብቅ ክትትል ለሽብርተኛው ሸኔ እንዲደርስ ታስቦ በተሽከርካሪ ሲንቀሳቀስ የነበረ 764 የብሬን ጥይት ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከአዲሱ ገበያ አካባቢ ተነስተው ወደ ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ሊንቀሳቀስ ወደ ተዘጋጀ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-A 32761 አ.አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር አይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ ለመጫን እየተዘጋጁ ባለበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

በወንጀሉ ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መጀመሩን የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ የሽብርተኞች ተላላኪ የሆኑ ግለሰቦች በከተማችን አዲስ አበባ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ለፀጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ተግባር አስፈላጊውን ጥቆማና መረጃ በመስጠት ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW