ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት ከ450 ሺሕ በላይ መጽሐፍ ተሰበሰበ

ሰኔ 26/2014 (ዋልታ) “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርኆት ቤተ መጽሕፍ ሲካሄድ በነበረው መጻሕፍት የማሰባሰብ ዘመቻ ከ450 ሺሕ በላይ መጻሕፍት መሰባሰቡ ተገልጿል።
ለአንድ ወር ሲካሄድ የነበረው መጻሕፍት የማሰባሰብ ዘመቻ የመጀመሪያ ዙር ማጠናቀቂያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርኃ ግብሩ ላይ መጻሕፍትን የለገሱት ግለሰቦችና ተቋማት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉና የተለያየ ይዘት ያላቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዘመቻው ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉና የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።
ቤተ መጻሕፍቱ ሀሳብን በውይይት የሚፈታ ወጣት ለማፍራት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
ወጣቱን አማራጭ ሳይቀርብለት መውቀስ ተገቢ አይደለም ያሉት ዲያቆን ዳንኤል አሁን ላይ የአብርኆት ቤተ መጻሕፍት በቀን እሰከ 10 ሺሕ ሰው እያስተናገደ ነው ብለዋል።
ቤተ መጻሕፍቱ የሚያስፈልገውን ያህል መጻሕፍት እንዲኖሩት አሁንም ዜጎች ልገሳቸውን ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬትን ጨምሮ በመጻሕፍት ማሰባሰብ ዘመቻው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም መጻሕፍት ያበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦችም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በመስከረም ቸርነት