ለአትሌቲክስ ቡድኑ አቀባበል ኅብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

ሐምሌ 20/2014 (ዋልታ) ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አቀባበል ኅብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብር ኃይል ጥሪ አቀረበ፡፡

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ውድድሩን በውጤት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል፡፡

በአቀባበሉ ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚደረጉ ኅብረተሰቡ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ተካፍለው አስደሳች ውጤት ላስመዘገቡት የአትሌቲክስ ቡድን አባላት ነገ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ደማቅ አቀባበል ይደረጋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑ ካረፈበት ስካይላይት ሆቴል ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ በአጀብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ስለሚጓዝ የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ይደረጋሉ።

ቡድኑ ከስካይ ላይት ሆቴል ተነስቶ በቦሌ ጎዳና ፣ መስቀል አደባባይ ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን ፣ ሂልተን ሆቴል ፣ ፓርላማ ፣ አራት ኪሎ ፣ ራስ መኮንን ድልድይ ፣ ፒያሳ ፣ ቸርችል ጎዳና ፣ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ብሔራዊ ቴአትር ፣ ሜክሲኮ አደባባይ ፣ ለገሃር ፣ መስቀል አደባባይ በማድረግ መዳረሻውን ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ያደርጋል።

ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ ሲሆን የአትሌትክስ ቡድኑ በአጀብ በሚያልፍበት ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም ከተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች በስተቀር የተጠቀሱት መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ ህዝቡ ይህን ተገንዝቦ የተለመደውን ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ወደ ቦሌ አየር መንገድ የሚመጡ መንገደኞችና ሌሎች ተጠቃሚዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ መገለጹን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

ከፀጥታ ጋር ተያያዥ መረጃ ወይም ጥቆማ ለመስጠት በ991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11፣ 01- 11- 26- 43- 59፣ 01- 11- 01- 02- 97፣ መጠቀም እንደሚቻል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።