ለአገር መከላከያ ሰራዊት በ105 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

ኅዳር 7/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአቃቂ ቃሊቲ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት በ105 ሚሊየን ብር የሚገመት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በዚህም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለአገር መከላከያ ሰራዊት 51 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ሐቢባ ሲራጅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የአሸባሪ ቡድኑን ግብዓተ መሬት ማፋጠን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አክለውም ይህንን ፈታኝ ወቅት በተባበረ ክንድ እንድናልፍ ከመነቃቀፍ ይልቅ መተጋገዝን አስቀድመን ልንሰራ ይገባል ማለታቸውን ባልደረባችን ሔብሮን ዋልታው ከስፍራው ዘግባለች፡፡

በተመሳሳይ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ54 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የክፍለ ከተማው አስተዳደር አስታውቋል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና አስፈፃሚ ሽታዬ መሀመድን ጨምሮ የክፍለ ከተማው አመራሮች ወረዳ 1 በነዋሪዎች እየተዘጋጀ ያለውን የስንቅ ዝግጅት ተመልክተዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ እየተደረገ ባለው ርብርብ በክፍለ ከተማው በገንዘብና በቁሳቁስ ከ54 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ዋና አስፈፃሚዋ ተናግረዋል፡፡

በድጋፍ አሰባሰቡ ሂደቱ ላይ እየተሳተፉ ላሉ የክፍለ ከተማው ማህበረሰብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኅብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊታችን እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እና ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላም የመጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መናገራቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡