ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ ተዘጋጀ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ የቴክኒክ እና ሙያ ሰልጣኞችን ብቃት በማዳበር ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል።

በመድረኩ ላይ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ተሳታፊ ሲሆኑ፣ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠናን ጥራት ለማሻሻል ብሎም ወደ ኢንዱስትሪ መር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረስ የሚያግዙ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል።

መንግስት የተማረው ሀይል የሀሳብ ልዕልና ያለውና በቴክኒክ ክህሎቱ የበለፀገ እንዲሆን የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ፖሊሲ ቀርፆ ወደ ትግበራ መግባቱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል፡፡

ፓሊሲው በቴክኒክ ክህሎት የተካኑ፣ በፈጠራ ብቃታቸው የበለፀጉና ለስራ ተነሳሽነት ያላቸውን ወጣቶች ለማስመረቅ ለኢንዱስትሪው ትልቅ ግብአት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዋችን በብቃት ለማሰልጠን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ማሰልጠኛ ተቋም መገንባት አስፈላጊ መሆኑ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፣ በዚህም ሰልጣኞች በኢንዱስትሪው ውስጥ ለአገልግሎት ሲሰማሩ በክህሎት የዳበሩ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል።

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሳደግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ብቁ፣ የሰለጠኑ እና በክህሎት የዳበሩ ሰልጣኞችን በማፍራት እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ጋር በማስተባበር የስራ እድልን መፍጠር መቻሉ አንድ እርምጃ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ዘርፉ አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግብ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ ጋር ያዘጋጀው የትስስር መድረክ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ይሞላል ተብሎ ይታሰባል።

በኢንዱስትሪዋች ውስጥ በብቃት የሚያገለግሉ ሰራተኞችን የሚያፈሩት የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲዎች ሲሆኑ፣ ውጤታማ የሆነ ሰልጣኝን ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማሸጋገር ብሎም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በአሰልጣኝ ኤጀንሲዎች እና በኢንዱስትሪዎች መካከል ትስስር ሊፈጠር እንደሚገባ ይታመናል።

(በቁምነገር አህመድ)