ለኢፈርት ድርጅቶች ገለልተኛ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ተሾመ

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቅራቢነት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በመ/ቁ 263499 ለኢፈርት ድርጅቶች ሰባት አባላት ያሉት ገለልተኛ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ሾሟል፡፡

ድርጅቶቹን በባለአደራነት እንዲያስተዳድሩ ከተሾሙት አባላት መካከል አምስት ሰዎች ከግል ተቋማት የተውጣጡ ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ ከገንዘብ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተውጣጡ መሆናቸውን የአፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደሩ አባላት ገለልተኝነት፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የሙያ ሥነ ምግባር እና ትላልቅ የንግድ ድርጅቶችን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት፣ በቦርድ አመራርነት እንዲሁም አባልነት በመምራት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ መሆናቸውን ዶክተር ጌዲዮን ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ድርጅቶችን ወደ ሥራ ማስገባት፣ በእያንዳንዱ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ከሚሰሩ ብዛት ያላቸው ሠራተኞች የሥራ ዋስትና ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍና የድርጅቶቹን ንብረት ከብክነት በመከላከል በአግባቡ ጠብቆ ለመያዝ እንዲያመች በጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር እንደሚመራም አመልክተዋል፡፡

ለኢፈርት ድርጅቶች ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር በመሾም ሂደት ውስጥ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የትግራይ ክልል ጊዜአዊ አስተዳደር ከፍተኛ ሙያዊ ድጋፍና አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አብራርተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፣ አባላቱ ጥናት ሲያደርጉ እንደቆዩና ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከአባላቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ባለአደራ አስተዳደሩ በፍርድ ቤት ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት የማስተዳደር ሥራን የሚያከናውን ሲሆን፣ በየጊዜው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሾመው ፍርድ ቤት እንዲሁም ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የማቅረብ ኃላፊነት ይኖርበታል ተብሏል፡፡

የቦርዱ አባላት ከዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና ከዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

(በትዝታ መንግስቱ)