ለዘመን መለወጫ በዓል የቄራዎች ድርጅት ዝግጅት

የቄራዎች ድርጅት

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) ህብረተሰቡ ህገወጥ እርድ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር አውቆ ከድርጊቱ እንዲታቀብ የአዲስ አበባ ከተማ ቄራዎች ድርጅት ጥሪ አቀረበ፡፡

ድርጅቱ መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል አስመልክቶ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለመጭው ዘመን መለወጫ በዓል በድርጅቱ ከ2 ሺህ 500 በላይ የዳልጋ ከብት፣ ከ1ሺህ 500 መቶ በላይ የበግና የፍየል እርድ የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በእርድ አገልግሎቱ ሉካንዳ ቤቶች ከሚያሳርዱት በተጨማሪ ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ለከተማዋ ነዋሪ የበሬ፣ ፍየልና በግ እንስሳት እርድ አገልግሎት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የስጋ መሸጫ ሉካንዳ አንድ የበግ ስጋ በኪሎ 210 ብር እንዲሁም አንድ የበሬ ስጋ በኪሎ 285 ብር የሚያቀርብ መሆኑን ኃላፈው ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚከናወኑ የህገ ወጥ እርድ ምክንያት በዓመት ከ1.3 ቢሊየን ብር በላይ ከዘርፉ የሚገኝ ገቢ እንደሚያሳጣ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

 

በሰለሞን በየነ