ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ ዝግጅቶች በከፍተኛ ርብርብ በመከናወን ላይ ይገኛሉ – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ግንቦት 18/2016 (አዲስ ዋልታ) የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኞች ተከላ እየተቃረበ እንደመሆኑ ዝግጅቶች በከፍተኛ ርብርብ በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንደገለጹት የተከላ ስፍራዎች ተለይተው በመዘጋጀት ላይ ሲሆኑ ችግኞችም በተከታታይነት በመፍላት ላይ ናቸው።

ዓመታዊ መርኃ ግብራችን የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነት መርህን የሚያስፋፋ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚከላከል፣ የደን ጭፍጨፋን ጉዳት የሚቀለብስ፣ የመሬት መራቆትን የሚቀንስ ሲሆን የማኅበረሰብ አባላት፣ ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት በጋራ በመቆም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎች እንዲተከሉ የተሰራበት ንቅናቄ ነው ሲሉም ገልጸዋል።