ለዜጎች ሰላምና ደህንነት ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ መሰጠት ይገባል ተባለ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የሰው ልጆች ሁሉ ሰላምን በእጅጉ የሚሹበት ጊዜ ላይ በመሆናችን ያለንን ሁሉ አቅም ተጠቅመን ሰላምን ለማረጋገጥ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም አሳሰቡ።

የፌደራል፣ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሰላምና የፀጥታ ተቋማት የሰላም ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጊሾ (ዶ/ር) ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ ለህዝቦች ህልውና እና ለሀገሪቱ ብልፅግና  በተለየ ሁኔታ የሚሰራበት ወቅት ነው ብለዋል።

በክልሉ ከዚህ ቀደም የሚታዩ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት ላለፉት ሶስት ወራት ምንም አይነት የፀጥታ ችግር አለመከሰቱን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው ለዜጎች የሰላምና ደህንነት ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ሰላም ለሁሉም የሚያስፈልግ ነገር ቢሆንም በጥቂቶች ሊደፈርስ እንደሚችል አስምረውበታል ሚኒስትሩ።

በመድረኩ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በአንድ ሰው ግድያ የተጀመረ ሲሆን ከ17 ሚሊየን በላይ ሰዎችን መንጠቁ እንዲሁም በሒትለር ጠብ አጫሪነት የተቀሰቀሰው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ60 እስከ 70 ሚለየን ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ በምሳሌት ተጠቁሟል።

በጥልቀት ሳይታሰብባቸው እና በድንገት ታቅደው የሚፈፀሙ የሰላም መደፍረስ ችግሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ቀድሞ መዘጋጀቱ ተገቢ እንደሚሆን የሰላም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የሀይማኖት አባቶች ዜጎች ለሀገር ሰላምና ደህንነት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አካሉ ጴጥሮስ (ከሚዛን አማን)