ለዜጎች የሚደረገው ጥንቃቄና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደነቅ ነው – የትግራይ ተወላጆች

የትግራይ ተወላጆች

በአዳማ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በመንግስት እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ሂደት እና በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እየተደረገ ያለው ጥንቃቄ እና የሰብዓዊ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ተወላጆቹ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ደህንነታቸው እና መብታቸው ተጠብቆ ለረዥም አመታት መኖራቸውን ያነሱት ተወላጆቹ አጥፊው የትህነግ ቡድን ላይ በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ) ፅንፈኛ ቡድንን መንግስት ለህግ ለማቅረብ እየሠራ ነው ያሉት የአዳማ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አለማየሁ ቱሉ በህግ የማስከበር ተግባሩ የትግራይ ህዝብ እና ትህነግ አንድ እንዳልሆኑ በተግባር የታየበት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በከተማዋ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ተዋደው እና ተከባብረው የሚኖሩባት እንደመሆኑ ይህ ሰላማዊ የሆነ አካሄድ ለማስቀጠል እንደሚሰራም ኃላፊዊው ተናግረዋል፡፡

የትህነግ ቡድን አባላትን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገው ሂደት በመደገፍ ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድሻውን መወጣት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

 

(በብዙአየሁ ወንድሙ)