ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ዛሬ ይካሄዳል

ሰኔ 15/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን ለማጠናከር በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል የመጀመሪያው የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በዛሬው ዕለት ይካሄዳል፡፡

የገቢ ማሰባሰቢያው “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን ይደግፉ፤ ወንድማማችነትን ያጠናክሩ” በሚል መሪ ቃል ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው፡፡

የገቢ ማሰባሰቢያው ከተመሰረተ የወራት ጊዜ ብቻ ያስቆጠረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አሁን የበጀት ጉድለት ያለበት በመሆኑ ከሌሎች ወንድም እና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ክልሉን ማጠናከር እና ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ ክልሉን ለማገዝ ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ክልሉ ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርቶች፣ የቡና እና የቅመማቅመም እንዲሁም የማዕድናት ሀብት ባለቤት ሲሆን በቱሪዝሙም ዘርፍ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የኮይሻ ፕሮጀክትን ጨምሮ ትልልቅ ፓርኮች በውስጡ ይዟል፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሩ የፌዴራል ተቋማት፣ ሁሉም ክልሎች፣ ኢንባሲዎች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች እንደሚሳተፉ ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ኅብረተሰቡ የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግም የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች ይፋ መደረጋቸውም ይታወቃል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW