ለጋራ መኖሪያ ቤት የወጣው እጣ ውድቅ ተደረገ

ሐምሌ 6/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ውድቅ አደረገ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ25 ሺሕ 491 ያወጣው የ20/80 እና 40/6 ላይ እጣ የወጣበት ሲስተም ላይ የተአማኒነት ጉድለት እንደነበር በመረጋገጡ ነው የወጣውን ዕጣ ውድቅ ያደረገው፡፡

በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ጉዳዩን ያጣራው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።

ከእጅ ንክኪ በፀዳ መልኩ እጣ የማውጣት ሥርዓቱ እንዲካሄድ በሚል በባለሙያ የለማው ሶፍትዌር ያልቆጠቡና ዘግተው የወጡ ሰዎች እንዲካተቱበት ተደርጓል ነው የተባለው።

የቆጠቡና ለዕጣው ህጋዊ የሆኑ ከባንክ ዳታቸው የተላከ ቤት ጠባቂ ሰዎች ቁጥር 79 ሺሕ ቢሆንም የእጣ ሲስተም ውስጥ እንዲገቡ የተደረገው 172 ሺሕ ሰዎች መሆናቸው በገለልተኛ አጣሪ የቴክኒክ ቡድን መረጋገጡ ተገልጿል።

ከባንክ ለቤቶች ኮርፖሬሽን የተላከው የ20/80 ቆጣቢዎች መረጃ ሲመሳከርም የባንክ 586 ሺሕ 244 ሲሆን ቤቶች ከባንክ ተላከልኝ ብሎ ያስገባው ዳታ 610 ሺሕ 260 በመሆን ልዩነት አስይቷልም ነው የተባለው።

የ40/60 ደግሞ ከባንክ የተላከው የቆጣቢዎች ዝርዝር 111 ሺሕ 224 ሲሆን ቤቶች ኮርፖሬሽን ከባንክ ተላከልኝ ብሎ ያስገባው ስም ዝርዝር 112 ሺሕ 400 መሆኑ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ ከሶፍትዌር ማልማት ሂደት ጋር በተያያዘ ሶፍትዌር አልሚና ተጠቃሚ ሳይለይ በአንድ አካል ብቻ የተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመግለጫቸው ቤት ከማግኘት ፍላጎት ባለፈ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳለውም ጭምር ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ባለሙያዎችና አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነውም ብለዋል።

የማጭበርበር ሂደቱ የተሳካው በአመራሮች እገዛ የተደረገለት በመሆኑ ነው ያሉት ከንቲባዋ ተቋማቶቻችን ላይ ሪፎርም ማድረግ እንዳለብን የተማርንበት ሲሉም አክለዋል።

ካለው ቆጥቦ ቤት ሲጠባበቅ ለነበረው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለገጠመን የተአማኒነት ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።

በቀጣይም አዲስ ሶፍትዌር ለምቶ እንደ አዲስ እጣው እንዲወጣ ይደረጋልም ነው ያሉት።

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ከዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው የኦዲት ሥራ የጀመረው ከተማ አስተዳደሩ በባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች መገኘታቸውን መግለጹ ይታወሳል::

በትዕግስት ዘላለም

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW