ለግሉ ዘርፍ እድገት የሚሆን የ25 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ እድገት የ25 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ፕሮጀክቱ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በጀርመን ዓለም ዐቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂአይዜድ) የተዘጋጀ ሲሆን ለ4 ዓመታት የሚቆይና ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሺሰማ ገብረሥላሴ የግሉ ዘርፍ በድህነት ቅነሳ ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ እየተደረገ ባለው ሀገራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የጀርመን መንግሥት በጂአይዜድ በኩል ለግሉ ዘርፍ እድገት ላለፉት ስድስት ዓመታት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ጥበቃን መሠረት ያደረገ ደረጃ እንዲኖራቸው በሥራ እድል ፈጠራና በኢንቨስትመንት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽኝና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጀርመን ኤምባሲና የጂአይዜድ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።