ሌ/ጀነራል መሀመድ ተሰማ መከላከያ ሠራዊት አገርን ከመፍረስ ታድጓል አሉ

ጥር 13/2014 (ጥር) ‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት በመስዋዕትነቱ ሕዝባችንን ከመከራ እንዲሁም አገራችንን ከመፍረስ ታድጓል›› ሲሉ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ ተናገሩ፡፡
ወታደራዊ መኮንኑ ከምስራቅ ዕዝ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም ‹‹አሸባሪዎቹን ትሕነግና ሸኔን ለመደምሰስ በተደረገው አገራዊ ርብርብ የሠራዊታችን አካል የሆነው የምስራቅ ዕዝ የሠራዊት አመራርና አባላት የከፈሉት መስዋዕትነት በሕዝባችን ላይ ተደቅኖ የነበረውን የኅልውና ስጋት በመቅረፍ ነፃነቱን ያጎናፀፈ ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደዕዙ ዋና አዛዡ ገለፃ በርካታ ከተሞችን በመቆጣጠር ሕዝብን ሲዘርፍና ሲገድል የነበረውን ሽብርተኛ በመደምሰስ፣ በመማረክና በማቁሰል ከፍተኛ የሆነ ሰብኣዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ የተረፈው ኃይሉም ወደ መደበቂያው እንዲሸሽ ተደርጓል፡፡
‹‹ሕዝባችን ከጎናችን ተሰልፎ ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ የድሉ ዋነኛ ምንጭ በመሆኑ በቀጣይም ሽብርተኛውን ትሕነግ እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ የሚያስችሉ ወታደራዊ ዝግጁነታችንን ማጠናከር ይገባል›› ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡