ልመናን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገራችን በማጥፋት ራሳችንን የቻልን ለመሆን እንትጋ- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – ልመናን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገራችን በማጥፋት ራሳችንን የቻልን ለመሆን እንትጋ ሲሉ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
ሚዛን አማን አረንጓዴ የለበሰች አካባቢ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አረንጓዴ ያለበሷት አባቶቻችሁ በመሆናቸው እናንተም የእነሱን አሻራ በመከተል ሚዛን አማንን አረንጓዴ አልብሱ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ወጣቶች ሀገራችሁን መጠበቅ አትዘንጉ እኛ ደግሞ የለመለመች ሀገር እናስረክባችኋለን ሲሉም አክለዋል፡፡
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፣ ባለፉት ሦስት አመታት የማይታሰቡ የሚመስሉ ሥራዎችን ሠርተው በማሣየታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
አክለውም የብልፅግና ጉዟችን የሚረጋገጥበት፣ የህዝብ ጥያቄ የሚመለስበት ጊዜ ላይ በመድረሳችን ደስ ብሎኛል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚዛን አማን አየር ማረፊያ የማስጀመሪያ መሰረት ድንጋይም አስቀምጠዋል፡፡
(በሜሮን መስፍን)