ልዩነታችንን ተቀብለን ሀገራችንን ማፅናት አለብን ሲሉ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) “ልዩነታችንን ተቀብለን ሀገራችንን ማፅናት አለብን” ሲሉ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

“ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው ፓናል ውይይት ዛሬ በጂግጂጋ ከተማ መጀመሩና የፎቶግራፍ አውደ ርዕይም መከፈቱ ይታወቃል።

ተመሳሳይ የፓናል ውይይት ከሚካሄድባቸው 11 ከተሞች መካከል አንዱ የሆነው የጂግጂጋውን መድረክ በይፋ ያስጀመሩት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ናቸው።

በዚህ ወቅት አፈ ጉባኤው እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዝቡ በሀገራዊ ጉዳዮች የሚያወያዮ መድረኮች በዋና ዋና ከተሞች ተዘጋጅተዋል።

“ኢትዮጵያ በማሸነፍ እንደምትቀጥል ለማሳየት የሚያስችሉና የህዝቡን አብሮ የመምከር ባህል የሚያጎለብቱ ህዝባዊ ውይይቶች ይደረጋሉ” ብለዋል።

ረጂም ታሪክ ያለን ሀገርና ህዝብ መሆናችንን ለአለም ለማሳየት ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል የሚሉ አካላት በእነዚህ መድረኮች ተገኝተው ሀገራችንን የሚጠቅሙ ሀሳቦች እንዲያካፍሉ ጥሪ መቅረቡንም ጠቁመዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የተዘጋጀው መድረክ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ታዳሚዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ በምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

መድረኩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና አርቲስቶች እንዲሁም ጋራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፣ ኦጋዞች፣ ሱልጣኖችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት”ስለኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተመዘገቡ ድሎችና ያለፉ ውጣ ውረዶችን እንደሚያሳይ የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡