ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት ይምጣ – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ሐምሌ 26/2015 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት እንዲመጣ ጥሪ አቀረቡ፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የፀጥታ ችግር ማጋጠሙን ጠቁመው መንገድ በመዝጋት የሰዎችን እንቅስቃሴ በመግታት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት። ያለው ግጭት እርስ በእርስ እያገዳደለና ሰብዓዊ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።

እርስ በእርስ መጠፋፋት ዘላቂ ችግር እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም ለሰላም መረባረብ አለብንም ብለዋል።

የክልሉ የፀጥታ መዋቅርና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀው የክልሉ ሕዝብ እየተደረገ ያለውን ሕግ የማስከበር ሂደት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተውጣጣ የኢትዮጵያዊያን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መከላከያን ያለ ስሙ ስም መስጠትና መተንኮስ አግባብ አይደለምም ብለዋል። የፀጥታ ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ሁሉም ጥያቄ አለኝ የሚል ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መረባረብ አለበት በማለት ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ለሰላም ዘብ በመቆም ችግሮቻችን መፍታት ይገባናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ክልሉን ዋጋ የሚያስከፍል ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ ሁሉም ለሰላም መረባረብ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

አሁን ያለው አካሄድ ክልሉን አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለሰላም እንዲሠራም ጠይቀዋል። እርስ በእርስ በመገዳደል ያመጣነው ለውጥ የለምም ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ ለሰላም በየአካባቢው ያለውን ትንኮሳ በማስቆም ሁሉም ወደ ሰላም እንዲመጣም ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።