ሕወሓት በታዳጊዎች ላይ የጦር ወንጀል እየፈጸመ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 29/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በታዳጊዎች ላይ የጦር ወንጀል እየፈጸመ መሆኑ ተገለጸ።

ታዳጊ ህይወት ሀዋዝ ባልጠበቀው ሁኔታ ዓድዋ ከወላጆቹ ጋር በሚኖርበት ቤት የቀበሌ አመራሮች ትፈለጋለህ ብለው ሲወስዱት እሱም ቤተሰቡም በጣም ደንግጠው እንደነበረ ይናገራል።

ህይወት ሀዋዝ ከሌሎች የአካባቢው ታዳጊዎች ጋር ወደ ግንባር ሲልኩት መቃወም ባይችልም አብሮ እንደማይዘልቅ ቀድሞ ወስኗል።

በዚህም ግንባር ላይ እያለ ከጦርነቱ ለማምለጥ ሲሞክር ተመቶ ቆስሎ መያዙን ተናግሯል።

በዚህ ዘመን የትግራይን ሕዝብ ፍትሐዊ ላልሆነ ጦርነት የዳረጉት አካላት በኅብረተሰቡ ላይ እየፈጸሙት ያለው ተግባር አሳፋሪ በመሆኑ ሕዝቡ ሊቃወማቸው ይገባል ብሏል።

ከሽረ እንዳሥላሰ የመጣው ታዳጊ ገብረሊባኖስ የማነ ደግሞ “ትግራይ ተወራለች፤ ነጻ ማውጣት አለብን” በሚል ከቤተሰቦቹ ነጥለው አስገድደው ወደ ጦርነት እንዳስገቡት ይናገራል።

የራሳቸውን ልጆች በተሻለ ሁኔታ እያኖሩ የድሃ ልጆችን ለሞት የሚዳርጉትን የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችን ሕዝቡ መታገል አለበት በማለትም ቁጭቱን ይገልጻል።

በጦርነቱ በርካታ ታዳጊዎች ሲጎዱ ቀሪዎቹ የተሳካላቸው ደግሞ ማምለጥ መቻላቸውን ገልጾ እሱም በአፋር በኩል ተገደው በገቡበት ጦርነት ሲሸነፉ መሳሪያውን ጥሎ ለማምለጥ ሲሞክር መያዙን ተናግሯል።

ከመቐለ ተገዶ ወደ ጦርነቱ የገባው ታዳጊ ገብረ አርአያ ደግሞ “መሳሪያ ከቆሰሉ ሰዎች ወይም ከመከላከያ ነጥቀን እንሰጣችኋለን” ተብለው በባዶ እጃቸው ወደ ጦርነቱ ሲገቡ ተደናግጦ ህይወቱን ለማዳን ሾልኮ ለማምለጥ ሲሞክር እንደተያዘም ያስረዳል።

“የአመራሮቹ ልጆች በሰላም ተቀምጠው እኛን አታለው ወደ ጦርነት ይዘውን ገብተዋል” የሚለው ታዳጊው ድርጊቱን ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ሊያወግዙት እንደሚገባ ተናግሯል።

በግንባሩ ኅብረሰተቡን በማስተባበር ሥራ ላይ የሚገኙት የክልሉ ማረሚያ ቤት ምክትል ኮሚሽነር አቶ መሐመድ አሕመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአሸባሪው ሕወሓትን የጥፋት ሴራ የማምከኑ ተግባር በተሳካ ሁኔታ ቀጥሏል።

“በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘው  አሸባሪው ሕወሓት እስትንፋሱን ለማራዘም ዛሬም ገና አጥንታቸው ያልጠነከረ ለጋ ታዳጊዎችን ከትግራይ እናቶች እየነጠቀ የጦርነቱ ሰለባ እያደረገ ይገኛል” ብለዋል።