ኅዳር 3/2014 (ዋልታ) ሆላንዳዊው ምሁር ጆን አቢንክ (ፕ/ር) በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዙሪያ በሰሩት ጥናት አሸባሪው ሕወሓት ጦርነቱን ከመቀስቀስ ጀምሮ ያደረሰውን ኢሰብኣዊ ድርጊቶችና ቀውስ አጋለጡ።
በኔዘርላንድስ (ሆላንድ) አፍሪካ ላይደን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና አስተዳድር ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪው ጆን አቢንክ (ፕ/ር) የውጭ ኃይላት ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በማበራቸው በንፁሀን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመውን ትግል በጥናታቸው ዳሰዋል።
የምዕራባዊያን ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን እያሰራጩ ያሉትን ሀሰተኛ ዘገባዎችን ተከትሎ አሜሪካና የምዕራቡ ጎራ የሚጠበቅባቸውን ፍትሓዊ ስርዓት እየተከተሉ አይደለም የሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል፡፡
ተመራማሪው ኢትዮጵያን በተመለከተ ሦስት ዳጎስ ያሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን “የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ፖለቲካ (2020-2021)፣ የጦርነት ሂደት፣ የመገናኛ ብዙኃን አድልዖ እና የፖሊሲ ትግል” በሚል ርዕስ የተለቀቀው ጥናት በመግቢያው አሸባሪው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ሰራዊት በማጥቃት ጦርነቱን እንደቀሰቀሰ መረጃዎችን እያጣቀሰ ያትታል፡፡
በፖለቲካ የሐሳብ የበላይነት ተሸንፎ ከአራት ኪሎ ወጥቶ መቀሌ የመሸገው አሸባሪው ሕወሓት “ለ27 ዓመት ወደ ነገሰበት ዙፋኑ ለመመለስ 200 ሺሕ ሰራዊት ሲያዘጋጅ እንደነበር” ጽሑፉ ጠቅሷል፡፡
የሽብር ቡድኑ የሰሜን ዕዝን አጥቅቶ ዳግም ወደ አራት ኪሎ ዙፋን ለመመለስ ዝግጅቱ በወታደራዊ ኃይል ዘርፍ ብቻም ሳይሆን ጥርሱን ከነቀለበት የፕሮፓጋንዳና የሳይበር ጦርነቶችም አንፃር ከፍተኛ ዝግጅት ያደረገበት ጉዳይ እንደሆነ ቡድኑ በምስጢር ካዘጋጀው ሰንድ ጋር ተጣቅሶ ቀርቧል።
ጸሐፊው ቡድኑ በእብሪት በከፈተው ጦርነት የምግብ ዋስትናን አሳጥቷል፤ ምጣኔሃብትን አውድሟል እንዳጠቃላይ አገሪቱን አደጋ ውስጥ ከቶ የቀጣናውን አለመረጋጋት ለበለጠ ስጋት ዳርጓል ሲሉ አስነዋሪ ባህሪውን አጋልጠዋል፡፡
የጆን አቢንክ (ፕ/ር) ጥናት መደምደሚያም የአውሮፖ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታትና አሜሪካ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ባላቸው ትስስር በ110 ሚሊዮን ሕዝብ ኅልውና ላይ እያደረጉት ያለውን ኃላፊነት የጎደለው ድራማ ኮንኗል።
በደምሰው በነበሩ