ሕገ ወጥነትን ለሚያጋልጡ የተዘጋጀ ሽልማት

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ)- ሕገ ወጥነትን ለሚጠቁሙ ሰዎች ጥቆማቸው ያስገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ የገንዘብ ሽልማትን በማበረታቻነት ሊሰጥ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
አስተዳደሩ ሕገ ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ በወጣ ደንብ ላይ ዝርዝር መግለጫ አውጥቷል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ በወጣ ደንብ ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ
ከለውጡ በፊት በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውጥንቅጦች በኢትዮጵያ ሕዝብና በቁርጥ ቀን ልጆቿ ትግልና መስዋትነት ለውጡን እውን በማድረግ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡
የከተማችን አስተዳደር ሌት ከቀን በርካታ የልማት ስራዎችን እየሰራ እና አሁን ሀገራችን የገጠማትን የውጭና የውስጥ ተጽኖ ለመመከት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው፡፡
ህዝባችን ለሀገር አንድነትና ሉዓለዊነት የውጭና የውስጥ ጫናን ለመመከት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጥቅም ብቻ ልቦናቸው የታወረና የኢትዮጵያን አንድንት ከማይፈልጉ ሃይሎች ጋር በማበር የሀገርን ክብር የሚያወርዱ ጠላቶችና እና ሆድ አደር ባንዳዎች ወቅታዊ የተፈጠረውን ችግር እንደአጋጣሚ በመጠቀም የከተማችን ሕዝብ የሚያማርር የኑሮ ጫና ለመፍጠር በርካታ ህግወጥ ተግባራትን እየፈጸሙ ነው፡፡
የከተማችን አስተዳደር ተከማችቶ የቆየውን ሕገወጥ እና የሌብነት ተግባር ለማጥፋት በተደራጁ ሌቦች ላይ ተገቢው እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ሆኖም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከነዋሪው ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እና እነዚህ ህገወጥ ተግባር ፈጻሚ ሌቦችን የሚያጋልጥ የከተማችን ነዋሪ ሊያበረታታ የሚያስችል የማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት ሕገወጥነትን መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የከተማው ካቢኔ ነሃሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ “ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ ደንብ” አውጥቷል፡፡
ይህ ደንብ በመደበኛ ሕጎች የሚፈጸሙት ተግባራት እንደተጠበቁ ሆኖ በቅርብ ጊዜያት እየተንሰራፋ የመጣውን ነዋሪውን የሚያማርሩ እና በመንግስትና በሕዝብ ንብረት ላይ የሚሰሩ ህገወጥ ተግባራትና ሌብነት ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል፡፡
ደንቡ ከለያቸው ዋና ዋና ህገ-ወጥ ተግባራት ውስጥ፡-
• የመሬት ወረራ፤ በመሬት ባንክ ተይዘው የነበሩ ይዞታዎችን ሕገወጥ በሆነ መንገድ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲወጣባቸው ማድረግ፤
• ሕገ-ወጥ ግንባታ፤
• የአርሶ አደር ይዞታዎችን በህገ ወጥ መንገድ ለማይገባው ሰው መብት እንዲፈጠር ማድረግ፤
• አላግባብ የመንግስት ቤቶችን፣ ሼዶችን፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና ሌሎች ማንኛውም የመንግስት ይዞታዎችን ወደ ግለሰብ ማዞር፤
• በመሬት፣ በመሬት ነክ እና በማናቸውም የከተማው አስተዳደር አካላት ላይ የተመደበ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመንግስት አግልግሎቶችን በገንዘብ መሸጥ፣ ጉቦ እና መማለጃ መቀበል፤
• በግልጽ ባለቤት ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ ተገንብተው ያሉ ሕንጻዎች እና ታጥረው የተያዙ ባዶ ቦታዎችን ይዞ መገኘት፤
• በስም ዝውውር መክፈል የሚገባውን የአሹራ፣ የቴምብር ቀረጥ፣ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ቀንሶ ማስከፍል፤
• መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችን በመደበኛ የንግድ መስመር እንዳይሸጥ መደበቅ፣ ማገድ ወይም መያዝ፤
• ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣
• በህገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ማዘዋወር፣
• የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገንዘቦችን በማተምና በማሰራጨት የማጭበርበር ወይም የማታለል ተግባር መፈፀም፤
• ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት አገልግሎት መቀበልና መስጠት እና ሌሎች በወጣው ደንብ የተዘረዘሩ ናቸው፤
ደንቡ ጥቆማ የሚቀርብባቸው ሕገወጥ ተግባራት ከለየ በኋላ ጥቆማው በምን ዓይነት መንገድ መቅረብ እንደሚገባው የጥቆማ ወይም የመረጃ አቀራረብ ሥርዓት በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ተጨባጭ መረጃ ለሚያቀርቡ ጠቋሚዎች ወይም መረጃ አቅራቢዎችን ለማበረታታት ስለሚሰጥ ማበረታቻ ምጣኔ የሚገልጹ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ ማበረታቻው ተጨባጭ መረጃ ያስገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ በገንዘብ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ደንቡ ይህ ተግባር የሚያከናውን የስራ ክፍል፣ የጥቆማ ማቅረቢያ ማዕከሎችን እና በዚህ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞች፣ ኃላፊዎችና ጠቋሚዎች ስለሚኖርባቸው ኃላፊነት እና ተጠያቂነትንም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ጥቆማ ያለው ማንኛውም መረጃ አቅራቢ ከታች በተዘረዘሩ አማራጮች ጥቆማ ማቅረብ ይችላል፡፡
በነጻ የስልክ መስመር 9977
በአካል ከንቲባ ጽ/ቤት 4ኛ ፎቅ፣
በኢሜል acity4338@gmail.com
ስለሆነም አስተዳደሩ ይህን ደንብ በሕዝብ ተሳትፎ በማስፈጸም ጤናማ የከተማ ሕይወትን የሚያውኩ፤ የሕዝብ ሀብት በሆነው የከተማ መሬት፣ ይዞታና ቤት ላይ ያለአግባብ ለመበልጸግ የሚጥሩትን በአጠቃላይ በከተማችን እየተስተዋለ ያለውን ሕገወጥ ተግባር በጋራ እንከላከል ሲል ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ነሐሴ 26 ቀን 2013
አዲስ አበባ