መላው የአማራ ሕዝብ በአሸባሪው ትህነግ ላይ ክንዱን የሚያሳርፍበት ጊዜው አሁን ነው – የአማራ ክልል

ሐምሌ 30/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶክተር) ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን ዘመቻ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኀላፊው በመግለጫቸው እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም በመጣስ ወረራ ፈጽሟል፡፡
አሸባሪው ቡድን ዛሬም እንደ ትናንቱ የኢትዮጵያን ሰላም ከማይፈልጉ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገር ለማፍረስ በግልጽ ወረራ መፈጸሙን ነው ዶክተር ሰማ ያነሱት፡፡
በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ እንደሚያወራርድ በመዛት የቆየ አማራን የማጥፋት ህልሙን በገሃድ ለመፈጸም እንቅስቃሴ እያደረገ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ህልሙን ለማሳካትም አርሶ አደሮችን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ጭምር እያስገደደ ወደ ጦርነት እየማገደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት የክልሉ የጸጥታ ኀይል ከፌዴራል እና ከሌሎች ክልሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት በሚያካሂዱት ጦርነት በርካታ የጠላት ኀይል መደምሰሱን ጠቅሰዋል፡፡
አሁንም ይህንን ወራሪ እና አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያነሱት ኀላፊው ከነገ ጀምሮ ጠላትን ባለበት ለመደምሰስ እና የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ዝግጅት መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡
ራስን ለማዘጋጀት እና ለማጠናከር ሲባል የወገን ኀይል በወጣባቸው አካባቢዎች ጠላት አጋጣሚውን በመጠቀም የሕዝቡን ሀብት መዝረፉን ያነሱት ኀላፊው በቀጣይ ዕድሉን ቢያገኝ በሀገሪቱ ላይ የከፋ ጥፋት እንደሚያደርስ ሕዝቡ ተረድቶ እስከመጨረሻው እንዲፋለም አሳስበዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ጦርነት ለማድረግ በተንቀሳቀሰባቸው እንደ ጉራ ወርቄ፣ ሀራ እና ዋግ አካባቢዎች አርሶ አደሩ ባደረገው ውጊያ በጠላት ላይ የፈጸሙትን ጀብዱ በሌሎች አካባቢዎችም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ነፃነት እና ክብር ያለመስዋእትነት እንደማይገኝ በመገንዘብ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የህልውና ዘመቻ የተቀናጀ ማጥቃት እንደሚካሄድና ሁሉም እንዲነሳ አሳስበዋል፡፡
ባለሃብቶችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ለሚደረገው የህልውና ዘመቻ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መላው የአማራ ሕዝብ በአሸባሪው ትህነግ ላይ ክንዱን የሚያሳርፍበት ጊዜው አሁን መኾኑን በመረዳት በአንድነት እንዲቆምም ጥሪ ማቅረባቸውን ከአሚኮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡