መረጃን መሰረት ያደረገ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የአመራርና የጤና ፋይናንስ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ዶ/ር ሊያ ታደሰ

መጋቢት 9/2015 (ዋልታ) የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥና መረጃን መሰረት ያደረገ የሕክምና አገልግሎትን ለመስጠት የአመራርና የጤና ፋይናንስ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር 59ኛ ዓመታዊ ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ እያካሄደ ሲሆን በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ማህበሩ ለጤናው ሥርዓት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩም በአገር ደረጃ ያለውን የጤና ሥርዓት ለማጎልበት የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመቅረጽ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች ተነሳሽነት ያላቸው ብቁና ሙያዊ ሥነ ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የተለያዩ ኮርሶችን በማዘጋጀት ተደራሽነትን በማሻሻል በብቃት ማረጋገጥ እና በስልጠና አቅራቢነት እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመንግስትም ሆነ በግል ጤና ተቋማት የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን ማዘመን እንደሚገባና ለዚህም የሙያ ማህበራት የሕክምና ባለሙያዎች የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና የሚዲያ ተቋማት በተቀናጀ መንገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡