መተከል ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ችግሮች እየፈታች እንደምትሻገር ማሳያ ነች ተባለ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየፈታች እንደምትሻገር መተከል ማሳያ ነች ተባለ፡፡

ይህ የተባለው በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ያዘጋጀው 12ኛው ስለ ኢትዮጵያ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡

የፓናል ውይይቱን የመሩት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን ወያኔ ጠረፍ ለሆኑ አካባቢዎችና ክልሎች ቅጥያና አጋር የሚል ስም እየሰጠ የህዝቦችን መብትና የልማት ጥያቄ ሲነፍግ መቆየቱን አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ የህዳሴ ግድብ በቶሎ እንዳይጠናቁቅ የተለያዩ ሴራዎች ይፈፀም እንደነበር አንስተው ለውጡ ከታደጋቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የህዳሴ ግድብ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉን በማተራመስ ሀገር ለማፍረስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም በመድረኩ የተናገሩ ሲሆን ጥናታዊ እሴቶች እና ባህሎች የገጠሙ ፈተናዎች ለመሻገር መሳሪያ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በክልሉ አንፃራዊ ሰላም መኖሩንም ጠቅሰው ይህም የኢትዮጵያ አሸናፊነትን ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዋና አስፈፃሚ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው መተከል ኢትዮጵያ በብርቱ የተፈተነችበት ስፍራ እንደነበር አስታውሰዋል።

ጠላቶች ሀገር ለማፍረስ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚገንበት በዚሁ ስፍራ ንፁሀንን በመግደል የጥፋት ተልዕኮ ይፈፅሙ ነበርም ብለዋል።

የመተከል ዙሪያ የኢትዮጵያ ተምሳሌት የሆን የመሬት፣ የውሃ ሀብት፣ የማዕድንና ሌሎችም እምቅ አቅም ያለ መሆኑን ተከትሎም ሀገር ይህን አቅም እንዳትጠቀም ሴራ የሚጠነሰስበት ነበርም ያሉት።

ሆኖም ኢትዮጵያ ከሚያደሟት በላይ የሚደሙላት በርካቶች በመሆናቸው ፈተናዎችን ተሻግራ እዚህ ደርሳለች፣ ፈተናዎቿን እያሸነፈች እንደምትሻገር ማሳያ ነውም ብለዋል።

ልማት በተግባር በሚል እየተካሄደ በሚገኘው የፓናል ውይይት በውሃ ልማትና የህዳሴ ግድብ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነት፣ሰላም ፣ልማት እና ማንነት ላይ ያተኮሩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ነው።

ትዕግስት ዘላለም (ከመተከል)