መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ ነው – ቢልለኔ ስዩም

ቢልለኔ ስዩም

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ያፀደቀው የሰላም ምክረ ሃሳብ መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡

ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ የሰጡት ኃላፊዋ መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት በማሰብ የተኩስ አቁም በመጪዎቹ ሳምንታት እንዲደረስ ያለውን ቁርጠጥነት በሰነድ ማረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

በሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ይህ ሰነድ መንግሥት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አመላካች ነውም ብለዋል፡፡

የሰላም ውይይት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ የሚያስፈልገው አይደለም ያሉት ኃላፊዋ የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት እስረኛ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡

ሕወሓት ፍላጎቱን ለማስፈፀም በትግራይ ክልል የኃይል አማራጮችን በተከታታይ እየተጠቀመ እንደሚገኝ ያወሱት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ቡድኑ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም ጭፍጨፋዎችን እንደሚፈፅም አመላክተዋል፡፡

ሕወሓት በህገወጥ መንገድ የሰበሰበውን የውጭ ምንዛሪ፣ ለመጠባበቂያነት የተቀመጡ የነዳጅ፣ የምግብና የመሳሰሉ ግብአቶችን ለዚሁ እኩይ ተልዕኮው እንደሚጠቀምም ጨምረው ገልጸዋል።

ሕወሓት ይህን ሁሉ እኩይ ተግባራት እየፈጸመ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሁኔታውን በሆደ ሰፊነት እየተከታተለ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከጦርነቱም በፊት፣ በጦርነቱ ወቅት እና ከጦርነቱም በኋላ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ እንደቆየ ያስታወሱት ኃላፊዋ በሕወሓት በኩል ለሰላም አማራጭ የተሰጠ ሥፍራ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ሕወሓት አሁንም በዚሁ ባህሪው መቀጠሉን አብራርተዋል።

ሕወሓት የሀሰት ክሶችን በማንሳትና የተሳሳቱ ትርክቶችን በመንዛት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት ሙከራ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ዙሪያ ስላለው ሁኔታ ብዥታ ሊኖር እንደማይገባ ያወሱት ቢልለኔ በክልሉ መልሶ ግንባታና መሰረታዊ ድጋፎች ላይ መንግሥት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት ባለሙያ በመላክም ሆነ እዛው ያሉውን የሰው ኃይል በመጠቀም በክልሉ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ለመመለስ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው ይህንን ለማድረግ አንዳንድ በመሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ መንግሥት እንደሚፈልግም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ለሚካሄድ የሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ መንግሥት በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የሰላም ንግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW