መንግሥት በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ድምዳሜዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት 24/2016 (አዲስ ዋልታ) መንግሥት በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ድምዳሜዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን በአዲስ አበባ አስጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በጦርነት እያለፈች እና በርካታ ስብራቶች እየገጠሟት ያለች ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።

ከዚህ የጦርነት እና የስብራት ታሪክ ለመውጣት ምክክር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም በንግግራቸው አስምረውበታል።

“ዛሬ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ነው” በዚህ አዲስ ምዕራፍ ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን በማጠናከር፣ መጓደልን በመሙላት ኢትዮጵያን ተስፋ ያላት ሀገር ማድረግ የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በታሪክ ሂደት ተደጋግሞ የማይገኘውን ይህንን ታሪካዊ የምክክር አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ሁላችንንም አሸናፊ ያደርገናል፤ በመሆኑም የትኛውም አካል ይህ የምክክር እድል እንዳያመልጠው ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ላይ በምንም ሁኔታ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኑን የሚመሩት ኮሚሽነሮችም በካበተ እውቀታቸውና ተሞክሯቸው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስራ ከመስራት ውጪ ሌላ ፍላጎት የላቸውም ሲሉም በኮሚሽነሮቹ ላይ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

በምክክሩ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎች ለማስፈፀም መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው የማንስማማባቸው አጀንዳዎች የሚገጥሙን ከሆነም በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት ያገኛሉ ብለዋል።

ሕዝብ ከወሰነ በኋላ ማናችንም ብንሆን የሕዝቡን ውሳኔ ማክበር ይኖርብናል ማለታቸውንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በኃይል አማራጭ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ጊዜያዊ አሸናፊና ተሸናፊ ፈጥሮ ከማለፍ በዘለለ ለችግራችን ዘላቂ መፍትሄ አያስገኝም ኢትዮጵያ እያካሄደቸው ባለው ምክክር የሚከስር እንደሌለ ገልፀው በሂደቱ ሀገር አሸናፊ ትሆናለች ብለዋል።