መንግሥት በመላ ሀገሪቱ በተካሄደ የሕግ ማስከበር ሥራ የበርካታ የሽብር ቡድኖች ኔትወርክ መበጣጠስ ተችሏል አለ

ሰላማዊት ካሳ

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) በመላ ሀገሪቱ በተካሄደ የሕግ ማስከበር ሥራ የበርካታ የሽብር ቡድኖች ኔትወርክ መበጣጠስ ተችሏል ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በተወሰደው ሕግ የማስከበር ሥራ ለሀገር ኅልውና አደጋ የሆኑ ወንጀሎችን ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ፣ የገንዘብ ዝውውር ኮንትሮባንድ እና መሰል ሕገ ወጥ ሥራዎችን መቆጣጠር መቻሉን ነው የገለጹት ።

በኦሮሚያ ክልል አሸባሪው ሸኔ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን ቡድኑን ከሕዝቡ የመለየትና የቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የማሳወቅ ሥራ መሰራቱንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት የህግ የበላይነት የማስከበር ሥራ ተሰርቷልም ነው የተባለው።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ በሶማሊያና ኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች በአልሻባብ የሽብር ቡድን ላይ እርምጃ መወሰዱንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

አልሻባብ፣ ሕወሓት እና ሸኔ የፈጠሩትን ኔትወርክ በመበጣጠስ የሀገር ኅልውና ላይ አደጋ የሆኑ የሽብር ወንጀሎችን ማክሸፍ መቻሉንም ገልጸዋል።

በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ሆነው ያልተገባ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ የጸጥታ አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

በሕግ ማስከበር ሂደቱ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውሰዋል።

በመስከረም ቸርነት

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW