መስከረም 21/2014 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው መንግሥት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያዘዛቸው የተባበሩት መንግሥታት 7 ሰራተኞች ውሳኔ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ከተሰማሩበት ዓላማ ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው በተገኙት ላይ የወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን የማስፈን ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ የትኛውም ተቋምና ግለሰብ ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ ሲንቀሳቀስ ከተገኘ ተግባሩ ሕገ ወጥ ነው፤ በ72 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ በታዘዙት ግለሰቦች ላይም የሆነውም ይሄው ነው፡፡
“አንዳንዱ ለሕክምና ሥራና ለጤና አገልግሎት ይመጣና፣ ጤናን በሚያዛቡና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ተግባራት ላይ ይሰማራል፡፡ ለውሃ ቁፋሮ ይመጣና አገር ሲቆፍር ይውላል፡፡ ይህ ዓይነት ተግባር ደግሞ በየትኛውም አገር አይፈቀድም” ብለዋል አምባሳደር ዲና ለኢፕድ በሰጡት ማብራሪያ፡፡