መንግሥት የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ዓለም ባንክ ገለፀ

የካቲት 27/2014 (ዋልታ) መንግሥት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን በማቋቋም የሥልጠና ጥራትን ለማሻሻል እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በዓለም ባንክ ትምህርት ዘርፍ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ሳፋ ኤል ኮጋሊ ገለፁ፡፡

ዳይሬክተሯ የቴክኒክና ሙያና ሥራ ዕድልን አሰመልክተው ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ሳፋ ኤል ኮጋሊ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን በማቋቋም ለሚኒስቴሩ ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቶ በቴክኒክና ሙያው ዘርፍ ጥራትን ለማስጠበቅ እና ብዙ ሥራዎች እንዲፈጠሩ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናው በሥራ ገበያው የተቃኘ እንዲሆንና ለወጣቶችም የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብን ለማስረፅ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት አማካኝነት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትብብር ሥራቸውን በማጠናከር ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።