መስከረም 13/2015 (ዋልታ) የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ልምድ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደሚያስፋፋ ገለፀ፡፡
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ስራ እና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎቿን ያካፈለችበት ውይይት በኒውዮርክ ተካሂዷል።
ከ77ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግስት ከመንግስታቱ የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግር አድርገዋል።
በዚህም አረንጓዴ አሻራ የቀጣናው ሀገራት አንድ የትብብር መስክ እንዲሆን ኢትዮጵያ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዓለም አየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ልማት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መደቀኑን ገልፀዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ በሁሉም ደረጃ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን አስተባብሮ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል እና የማጣጣም ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
ግላስኮ ላይ ተካሂዶ በነበረው 26ኛው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ እ.ኤ.አ እስከ 2030 የደን ምንጣሮ እና የመሬት መራቆትን ለመቀልበስ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ኢትዮጵያ 22 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬትን እንዲያገግም ለማድረግ እንዲሁም የደን እና የብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ ቃል በገባችው መሰረት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በአብነት አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩ 20 ሚሊየን ህዝብን በማሳተፍ ባለፉት አራት ዓመታት ከ25 ቢሊየን በላይ የዛፍ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።
አረንጓዴ አሻራ የቀጠናው ሃገራት አንድ የትብብር መስክ መሆን እንዳለበት ያመለከቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ በመከላከሉ ረገድ የቀጣናው ሃገራትን ትብብር ለማጠናከር ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነትን ወደ ጎረቤት ሃገራት ለማስፋት ጭምር እየሰራች ነው ” ብለዋል።
ባለፈው ዓመትም በጎረቤት ሃገራት የዛፍ ችግኞች እንዲተከሉ መደረጉን አስተውሰው በተመሳሳይ በተያዘው አመትም እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በኢኒሼቲቩ የተቀመጡ አላማዎችን ለማሳካት ከዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ከሆኑ አጋር አካላት ጋር ኢትዮጵያ በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥልም አመልክተው የልማት አጋሮች ኢንሼቲቩን ኢንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስታቱ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት አሁና ኢዛኮኑዋ በተወካያቸው በኩል ባደረጉት ንግግር የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ የእስካሁን ስኬት ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት እቅዶችን በተሳካ ሁኔታ የመፈፀም አቅሟ ከፍ ያለ ደረጃ መድረሱን ያመላከተ ነው ብለዋል።
ዘላቂነት ያለው የአረንጓዴ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ በኢትዮጵያ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ለሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ሆኖ መወሰድ አለበትም ብለዋል።
ተመ ይህን ተሞክሮንም ወደ 10 የአፍሪካ ሀገራት እንደሚያስፋፋ ነው ያመለከቱት።
ሌላው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአረንጎዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) መርሃግብሩ አዳዲስ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።