መንግስት በተናጠል የወሰደው የተኩስ አቁም ስምምነት በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተቀባይነትን ያገኘ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር


ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) –
መንግስት በተናጠል የወሰደውን የተኩስ አቁም ስምምነት የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ መደገፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
መንግስት ከትግራይ ክልል የሀገሪቱ ክፍል ሰራዊቱን ማስወጣቱና የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ መወሰኑ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን ጫና እሚያቆሙበትን እድል እንደፈጠረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ገልፀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገሪቱን ሳምንታዊ የውጭ ግንኙነት የስራ ክንዋኔዎች ባብራራበት መግለጫ፣ መንግስት ከሰሞኑ የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ጫና ሲያደርስ በነበረው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ በበጎ እየታየ እንደሆነ ነው የተገለፀው።
መንግስት የጥፋት ሀይሉ ህወሀት ለሀገር ስጋት በማይሆነበት ደረጃ በመሆኑ ጦሩን ከትግራይ ክልል ያስወጣበት ውሳኔ መልካም ውጤቶች እያስገኙ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ውሳኔውን የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት አድንቀውታል ብለዋል።
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ሱዳንና ግብፅ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በድርድሩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ያቀረቡት ደብዳቤ ውድቅ እንደተደረገ ተነስቷል።
የፀጥታው ምክር ቤት በሰጠው ምላሽም የአባይ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ በባለጉዳዮቹ አገራት መፍትሄ እንዲያገኝና፣ ግድቡም የልማት ጉዳይ በመሆኑ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለው ምላሽ ሰጥቷል ነው የተባለው።
በተለያዩ የአለም ክፍል ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም 200 ሺህ የሚጠጋ የገዘብና የቦንድ ግዥ ድጋፍ መገኘቱን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።
በፐብሊክና ዜጋ ተኮር ስራም በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ እያሳዩት ያለው ተነሳሽነት መጨመሩ በመግለጫው ተነስቷል። በሳምንቱ ጥቂት ቀናት ብቻም ከአረብ አገራት 9ሺህ 974 ዜጎች ወደ ሀገር ቤት እንደገቡ በመግለጫው ተወስቷል።
(ደምሰው በነበሩ)