መንግስት በትግራይ ክልል ያሰራጨው መድሃኒት ለታካሚዎች እፎይታ ፈጥሯል – የህክምና ባለሙያዎች

መንግስት በትግራይ ክልል ያሰራጨው መድሃኒት ለታካሚዎች እፎይታ መፍጠሩን የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ለትግራይ ክልል የላካቸው መድሃኒቶች ለታካሚዎች እፎይታን የሰጡ፣ ሃኪሞችንም ከጭንቀት የገላገሉ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው ወደ ትግራይ የላካቸው መድሃኒቶች እና የህክምና ቁሳቁሶች በመቀሌ ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት በመሰራጨት ላይ ናቸው።

ለኢዜአ አስተያየታቸው የሰጡ የህክምና ባለሙያዎች ቀደም ሲል በከተማዋ የመድሃኒት አቅርቦት በመስተጓጎሉ ህሙማን ለከፍተኛ ጭንቀት ተዳርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የዓይደር ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመድሃኒት ቤት ሃላፊ ሃሊማ አህመድ ከፌዴራል መንግስት የተላኩ የተለያዩ መድሃኒቶችን መረከባቸውን ገልጸዋል፡፡

የመድሃኒት አቅርቦቱ ሆስፒታሉ የነበረበትን የመድሃኒት እጥረት ችግር የሚፈታ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የሆስፒታሉ ፋርማሲስት አበባ ገብረሚካኤል ህሙማን ከሆስፒታሉ በነጻ የሚያገኟቸውን መድሃኒቶች ከውጪ በውድ ዋጋ ሲገዙ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን መንግስት መድሃኒቶቹን በማቅረቡ ችግሩ መፈታቱን ተናግረዋል።

“የመድሃኒት አቅርቦቱ የታካሚዎችን ችግር ከመፍታት በተጨማሪ ሃኪሞችም ለማህበረሰቡ በቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል” ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት በአስቸኳይ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ለክልሉ ህዝብ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በማሟላቱ የህክምና ባለሙያዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የፌዴራል መንግስት ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን መድሃኒቶችን በመቀሌ ከተማ ለተለያዩ የጤና ተቋማት ማሰራጨቱ ታውቋል።