መንግስት ከሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ጋር ለሚተባበሩ አካላት የመጨረሻ ማሳሰቢያ ሰጠ

መንግስት ከሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ጋር ለሚተባበሩ አካላት የመጨረሻ ማሳሰቢያ መስጠቱን አስታወቀ።

ሕገ መንግሥቱን እና ሌሎች የሀገሪቱን መሠረታዊ ሕጎች በመጣስ በሕወሐት ውስጥ የበላይነቱን የያዘው ቡድን፣ የሀገር አለኝታ እና ኩራት በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የኃይል ጥቃት መሰንዘሩ መንግስት አስታውሷል።

ከዚህ ጥቃትም አስቀድሞ፣ የጥቃቱ ጠንሳሽ የሆነው ቡድን፣ የሀገርን ሰላም እና የሕዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራትን ሲፈጽም ነበር ብሏል መንግስት ባወጣው መግለጫ፡፡

ይህ ሕገ ወጥ የሕወሐት ቡድን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በፈጸማቸው የጥፋት ተግባራት የሰላም መደፍረስ፣ የዜጎች ሞት እና መፈናቀል እንዲሁም አካባቢያዊ መናጋት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት ያሳየውን ትእግሥት እንደ ድክመት በመቁጠር ሕገ ወጡ የሕወሐት ቡድን ሀገርን የመድፈር ወንጀል ፈጸመ፡፡

በተለይም በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የተፈጸመው ሰፊ ጥቃት ሊታለፍ የማይችል እና የሀገርን ህልውና የሚፈታተን ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ መንግሥት ተገቢን ሕግ የማስከበር ርምጃ እንዲወስድ የሚያስገድድ ቅርብና ግልጽ አደጋ የደቀነ ነበር፡፡

እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጠር መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ተገቢውን ሕግ የማስከበር ርምጃ የመውሰድ የሞራል እና የሕግ ግዴታ እንዳለበት እሙን ነው።

ይህንን ግዴታውን ለመወጣት የፌደራል መንግሥት በሕወሐት ሕገ ወጥ ቡድን ላይ የሀገሪቱ ሕግ የሚያዘውን ርምጃ ወስዷል፡፡

በዚህ ርምጃም ከሀገር አልፎ ለቀጣናው ሥጋት ሆኖ የቆየው የሕውሐት ሕገ ወጦች ቡድን ከፍተኛ ወታደራዊ ዐቅም እና ዝግጁነት ተደምስሷል።

የዚህ ቡድን ቁልፍ አመራር የሆኑት ግለሰቦች ከፊሎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ዐቅማቸው እና ኃይላቸው እጅጉን ተዳክሞ፣ ከሕግ በመሸሽ የሚባዝኑ የፍትሕ ተሳዳጆች ሆነዋል።

በክልሉ በሕገ መንግሥታዊ አግባብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል። የፌደራል መንግሥትም አጥፊው ቡድን በቀስቀሰው ግጭት የደረሰውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም እየሠራ ይገኛል።

ይህ የመልሶ ግንባታና የማቋቋም ሥራ የሁሉንም ርብርብ እና እገዛ የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደርግ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የደረሰውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ለመቀነስ እና ክልሉን በተሻለ የአስተዳደር እና የልማት ቁመና ላይ ለማድረስ የማይተካ ሚና ካላቸው ተዋንያን ዋነኛዎቹ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከእነዚህ ዜጎች አንዳንዶቹ በሕውሐት ፕሮፖጋንዳም ሆነ በሕገ ወጡ ቡድን አስገዳጅነት ነፍጥ አንግበው በውጊያ ሜዳ ላይ እስከመሰለፍ ደርሰዋል፡፡

ነገር ግን እነዚህ የክልሉ ተወላጆች ዋነኛው የጥፋቱ ጠንሳሽ እና ባለቤት አለመሆናቸውን መንግሥት ይገነዘባል። ከዝርፊያው እና ከምዝበራው ተካፋይ ያልነበሩ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ የክልሉ ተወላጆች በአጥፊው ቡድን ጎትጓችነት እና ቅስቀሳ ከመንግሥት ጋር ተቃርነው፣ መሣሪያ ታጥቀው የተሰለፉ ቢሆንም እንኳን መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት ማየት እንደሚገባው ያምናል።

በመሆኑም የሀገር አንድነትን ለማጠናከር እና አጥፊው ቡድን ያፈረሳቸውን የጋራ እሴቶቻችንን፣ አብሮነታችንን እና መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የተለያዩ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን መንግሥት ያምናል፡፡

በመሆኑም፣ በሕገ ወጥ ጥቃቱ እና ተያያዥ በሆኑ የወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩ እና በዚም መነሻ የፍርድ ቤት መያዣ ከወጣባቸው ከፍተኛ የሕውሐት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ፤ ይህንንም እውን ለማድረግ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እና መኖሪያቸው በመመለስ ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀርባል።

በዚህ መንገድ ከአጥፊው ቡድን ተለይተው ወደሰላማዊ ኑሯቸው የሚመለሱ የክልሉ ተወላጅ ዜጎች፣ የትኛውም የሕግ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው፣ ከአጥፊ ተግባራት ተቆጥበው፣ ወደ ሥራቸው እና ኑሯቸው በሰላም መሠማራት ይችላሉ።

እነዚህን ዜጎች በመልካም ሁኔታ በመቀበል እንዲተባበሩ እና የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ለየሚመለከታቸው የጸጥታ፣ የአስተዳደር እና የሕግ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊው መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።

የጥፋት ቡድኑ አካል ሆነው በተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የፍርድ ቤት መያዣም የወጣባቸው ከፍተኛ የሕውሐት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች፣ በሰላም እጃቸውን ለሕግ አስባሪ ተቋማት እንዲሰጡ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።

እነዚህ አመራሮች እስከዛሬ ከደረሰው ሀገራዊ ጥፋት እና ጉዳት በመማር፣ ለፍትሕ ራሳቸውን በማቅረብ፣ ተጨማሪ ሀገራዊ ኪሣራ እንዳይደርስ እና በከንቱ የዜጎች ደም እንዳይፈስ የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ መንግሥት ጥሪ ያቀረበው።

ይሄንን የሚያደርጉ ከፍተኛ የሕወሐት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ራሳቸውን ከከፋ ቅጣት፣ ወገናቸውን ከመጎሳቆል ይታደጉታል ሲል ነው ጥሪው ያቀረበው፡፡

ይሄንን የመጨረሻ ጥሪ ተጠቅመው ራሳቸውን ለፍትሕ በማያቀርቡ የሕወሐት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ግን ሕግ በሚፈቅደው ሁሉም ዓይነት መንገድ፣ ሕግ ለማስከበር ሲባል፣ አስፈላጊው ሁሉ የሚፈጸም ይሆኗል ብሏል መንግስት