መገናኛ ብዙሃን የቋንቋ ተደራሽነታቸውን በማስፋት እውነታውን ለዓለም ማሳየት እንዳለባቸው ተገለጸ

ሐምሌ 30/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የቋንቋ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ትክክለኛውን የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም እንዲያሳዩ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ምሁራን ገልጸዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህራን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ በኩል ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ከውስጥና ከውጭ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው አገር ለማዳን አንድነትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች እያደረሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ መገናኛ ብዙሃኑ የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ይህም የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን አረዳድ በማስቀየር በኩል የተጫወቱት ሚና ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።

የሚስተዋለው ክፍተት ከሚጠቀሙበት ቋንቋ፣ ከሚያሰራጩበት አውታር እንዲሁም መረጃ ከመቀበልና ከማሰራጨት ተደራሽነት ጋር አያይዘው አስረድተዋል።

ይህ አካሄድ የዲፕሎማሲና የተግባቦት ስርዓቱ ላይ ጫና አለው ያሉት ዶክተሩ መገናኛ ብዙሃኑ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ዘገባዎቻቸውን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ መቅረፅ እንዳለባቸው መክረዋል።

ምዕራባዊያኑ የመገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛውን ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን እነሱ የሚፈልጉትን የማንፀባረቅ አካሄድ አላቸው ያሉት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም ተስፋዬ ናቸው።

እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ አወሳሰዳቸውና እይታቸው እንዲሁም ትክክለኛውን መረጃ ከተገቢው ምንጭ መውሰድ ላይ ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛውን የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ የማሳየት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሙያን መሰረት በማድረግ የተሳሳተውን አረዳድ ለማሳወቅ የቋንቋ ተደራሽነታቸውን በማስፋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።