መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ዘገባቸው ከገለልተኝነት ባለፈ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ

የኢዜማ እጩ ተወዳዳሪ ግርማ ሰይፉ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – መገናኛ ብዙሃን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች እና ወቅታዊ ፕሮግራሞች ገለልተኛ ከመሆን ባለፈ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊዘጋጁ እንደሚገባ ፖለቲከኞች አሳሰቡ።

ሙያተኞች ሥራቸውን በኃላፊነት መስራት እንጂ አክቲቪስት ጋዜጠኛ ሆኖ መቅረብ እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ እና የመገናኛ ብዙኃን ሚናን በሚመለከት ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢዜማ እጩ ተወዳዳሪ ግርማ ሰይፉ፣ መጪው ምርጫ ሕጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅጉን የላቀ ነው ብለዋል።

መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው ከምርጫ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች እና ወቅታዊ ፕሮግራሞች ማንኛውንም ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከማጥላላት የተቆጠቡ፣ ከግል አቋም የፀዱ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊ እና ትክክለኛ መሆን እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

መገናኛ ብዙኃኑ የተዛባ መረጃ ላለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያስገነዘቡት አቶ ግርማ፣ ከፌስ ቡክ ጋር ውድድር ገብተው፣ እኔ ቀድሜ ላቅርብ በሚል ፉክክር ያልተጣራ መረጃ በመስጠት እና በማቅረብ ዜጎችን ከማሳሳት መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ጋዜጠኞች ሙያዊ ሥነ ምግባርን ማክበር እና ለእውነት መቆም እንዳለባቸው ያስገነዘቡት አቶ ግርማ፣ በገለልተኛነት ሥራቸውን መሥራት እንጂ አክቲቪስት ጋዜጠኛ ሆኖ መቅረብ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል። ለዚህም መገናኛ ብዙኃንም ጋዜጠኞቻቸውን ማሰልጠን፣ መቆጣጠር አለፍ ሲልም ከሙያው ባፈነገጠ መልኩ ያልተገባ ተግባር በሚፈፅሙት ላይም አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለተፎካካሪ ፓርቲ መዘገብ እንዳለባቸው እና ፍትሐዊ እንሆናለን በሚል ሁሉንም መነካካት ተገቢ እንዳልሆነ አስታውቀው፣ ጠቃሚ እና ተፅእኖ መፍጠር የሚችለው የቱ ነው የሚለውን ለይቶ መምረጥ፣ መቃኘት እና መገምገም ግድ ይላቸዋል ብለዋል።

የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው በበኩላቸው፣ በቀደመው ሥርዓት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ደመወዝ ስለሚከፍላቸው፣ የገዢው ፓርቲ መገልገያ እንደነበሩ አስታውሰው፣ የሚከፈላቸው ደሞዝ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚሰበሰብ ግብር እንጂ ከመንግሥት ኪስ የተሰጠ እንዳልነበር ጠቁመዋል።

ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው

በአሁን ወቅት ኢትዮጵያም ይህን ምዕራፍ ዘግታ ወደ አዲስ ምእራፍ መሸጋገሯን ጠቁመው፣ ከአሁን በኋላ የመገናኛ ብዙኃኑ የገዢው ፓርቲ ድምፅ ማጉያ ሆነው መቀጠል እንደሌለባቸው አመልክተዋል።

በመጪው ምርጫም መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው ከምርጫ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች እና ወቅታዊ ፕሮግራሞች ማንኛውንም ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከማጥላላት የተቆጠቡ ከግል አቋም የፀዱ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ከዚህ በኋላም በምርጫ ምክንያት ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ያሳለፏቸውን በርካታ ቀውሶች መድገም እንደሌለባቸው እና በምርጫ ጉዳይ የአንድም ሰው ሕይወት ሊነጠቅ እንደማይገባ ያስገነዘቡት ዶክተር ሰይፈስላሴ፣ መገናኛ ብዙኃንም ሽፋን በሚሰጡበት ወቅት ነገሮች ከሚያባባስ፣ ከሚያጋጋል ሁኔታ መቆጠብ እና ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።