ሚኒስቴሩ ለተፈናቃዮች ከ736 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 28/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ አካላት ያሰባሰባቸውን ከ736 ሺሕ ብር በላይ የሚሆኑ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ልዩ ልዩ የቁሳቁስ ግብዓቶችን ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በሚኒስቴሩ የኮርፖሬት ሀብት አመራር ዳይሬክተር ጀነራል ሙሉጌታ እሸቱ በሰሜን ሸዋ ዞን በመገኘት ለዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ደረጀ ይንገሱ በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።

ድጋፉ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ ለተጎዱና ከቀያቸው ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች ግልጋሎት እንደሚውል ዋና ዳይሬክተሩ በድጋፍ ርክክብ ወቅት ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ቀደም ሲልም ከኅብረተሰቡ እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላትን በማስተባበርና ሀብት በማሰባሰብ በርካታ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ይህም ድጋፍ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዞኑ የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ በኩይት ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ ማኅበረሰብ እንዲሁም ከሀረሪ ክልል ማኅበረሰብ የተገኘ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል።

በድጋፉ ከተካተቱ ግብዓቶች መካከል የምግብ ዘይትና ማካሮኒን ጨምሮ ልዩ ልዩ የህፃናትና የአዋቂ አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣ ሞራሌ፣ ፋይዚት እና ሌሎችም ቁሳቁስ እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

የጽሕፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ደረጀ ይንገሱ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑን ጠቁመው ለተደረገላቸው ድጋፍ በተፈናቃይ ወገኖች ስም ከልብ አመስግነዋል።
ሆኖም ተፈናቃይ ወገኖች ወደቀያቸው እስኪመለሱና በዘላቂነት መቋቋም እስኪችሉ ድረስ ድጋፋችንን አበክረው ስለሚሹ በተለይም መጪው ጊዜ ክረምት እንደመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በየአቅጣጫው የጀመሩትን ሁለንተናዊ እገዛና ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።