ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የ5 ሚሊዮን ብር የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ አደረገ

የካቲት 17 2014 (ዋልታ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የ5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የዕለት ደራሽ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ድጋፉን ለሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሁሴን ሀሺ ቃሲም (ዶ/ር) አስረክበዋል።

በዘላቂነት የውሃ ልማትን በማጠናከር በየጊዜው የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በቀጣይ የተለያዩ የልማት ስራዎች ይከናወናሉም ብለዋል ሚኒስትሩ።

አሁን ላይ የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤

በክልሉ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመሻገር ሌሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።