ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የማዕድንና ነዳጅ ኩባንያዎች 50 ሚሊዮን ብር ሰብስቦ ለክልሉ አበረከተ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የማዕድንና ነዳጅ ኩባንያዎች የሰበሰበውን 50 ሚሊዮን ብር ለክልሉ አበርክቷል፡፡

ማዕድን የሀገርና የህዝብ ሀብት ነው ያሉት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ ኡማ ዋናው ተጠቃሚ መሆን ያለበትም ህዝብ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችም ከማእድንና ነዳጅ ሀብቱ በስራ እድልም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ መሆን ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

ገንዘቡ እንደ ትምህርት ቤት እና ጤና ተቋማት ያሉ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡